የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 12:22-50

ማቴዎስ 12:22-50 NASV

ከዚህ በኋላ በጋኔን የተያዘ ዕውርና ድዳ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ ኢየሱስም ፈወሰው፤ ሰውየውም ማየትና መናገር ቻለ። ሕዝቡም ሁሉ ተደንቀው፣ “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። ነገር ግን ፈሪሳውያን ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “ይህ ሰው አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ብቻ መሆን አለበት” አሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በእርሱ የተከፋፈለ መንግሥት ሁሉ ይወድቃል፤ እርስ በእርሱም የተከፋፈለ ከተማ ወይም ቤት አይጸናም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፣ እርስ በእርሱ ተለያይቷል ማለት ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል? እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በምን ሊያስወጧቸው ነው? ስለዚህ ልጆቻችሁ ይፈርዱባችኋል። እኔ ግን አጋንንትን የማስወጣው በእግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች። “ወይስ አንድ ሰው ወደ ኀይለኛ ሰው ቤት ገብቶ ንብረቱን ለመዝረፍ ቢፈልግ፣ አስቀድሞ ያንን ኀይለኛ ሰው ሳያስር እንዴት አድርጎ ይሳካለታል? ኋላም ቤቱን መበዝበዝ ይችላል። “ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ሁሉ ይበትናል። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ኀጢአት መሥራትና የስድብ ቃል ሁሉ መናገር ለሰዎች ይቅር ይባልላቸዋል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚነገር የስድብ ቃል ይቅር አይባልም። ማንም ሰው በሰው ልጅ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ይቅር ይባላል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ግን በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም። “ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ፣ መልካም ፍሬ እንድታገኙ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ መጥፎ ዛፍ ቢኖራችሁ ግን መጥፎ ፍሬ ታገኛላችሁ። እናንት የእፉኝት ልጆች፤ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ውስጥ የሞላውን አንደበት ይናገረዋልና። መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር በጎ ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር መጥፎ ነገር ያወጣል። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰዎች ስለ ተናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል። ምክንያቱም ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከቃልህም የተነሣ ይፈረድብሃልና።” ከዚያም አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ታምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። “ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ፣ ዕረፍት ለማግኘት ውሃ በሌለበት ደረቅ ቦታ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም። ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚያም ይሄድና ከራሱ የባሱ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ እነርሱም ሰውየው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።” ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው። ኢየሱስም፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰለት። በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች

Free Reading Plans and Devotionals related to ማቴዎስ 12:22-50