የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 4:1-15

የሉቃስ ወንጌል 4:1-15 አማ54

ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ። ዲያብሎስም፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ፦ እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው። ኢየሱስም፦ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መለሰለት። ዲያብሎስም ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ዲያብሎስም፦ ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል አለው። ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው፤ በመቅደስም ጫፍ ላይ አቁሞ፦ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፥ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ከዚህ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎአል አለው። ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ። እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር፥ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።