ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ እንደ ተመለሰ፣ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፤ በዚያም አርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ፤ በእነዚያም ቀናት ምንም ሳይበላ ከቈየ በኋላ በመጨረሻ ተራበ። ዲያብሎስም፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዘው” አለው። ኢየሱስም፣ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ብሎ መለሰለት። ከዚያም ዲያብሎስ ወደ አንድ ከፍታ ቦታ አውጥቶት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው፤ እንዲህም አለው፤ “የእነዚህ መንግሥታት ሥልጣንና ክብር ሁሉ ለእኔ ተሰጥቷል፤ እኔም ለምወድደው ስለምሰጥ፣ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል።” ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፏል” አለው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ ከቤተ መቅደሱም ዐናት ላይ አውጥቶ፤ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘ይጠብቁህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል፤ እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይጋጭ፣ በእጆቻቸው ያነሡሃል።’ ” ኢየሱስም፣ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሏል” ብሎ መለሰለት። ዲያብሎስ ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ ትቶት ሄደ። ኢየሱስም በመንፈስ ኀይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ወጣ። እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር ነበር፤ ሰውም ሁሉ ያመሰግነው ነበር።
ሉቃስ 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 4
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 4:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos