የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 23:1-25

የሉቃስ ወንጌል 23:1-25 አማ54

ሁሉም በሞላው ተነሥተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱትና፦ ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም፦ እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር። ጲላጦስም፦ አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም መልሶ፦ አንተ አልህ አለው። ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ፦ በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም አለ። እነርሱ ግን አጽንተው፦ ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በይሁዳ ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል አሉ። ጲላጦስ ግን፦ ገሊላ ሲሉ በሰማ ጊዜ፦ የገሊላ ሰው ነውን? ብሎ ጠየቀ፤ ከሄሮድስም ግዛት እንደ ሆነ ባወቀ ጊዜ ወደ ሄሮድስ ሰደደው፤ እርሱ ደግሞ በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም ነበረና። ሄሮድስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ስለ ሰማ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይመኝ ነበርና፥ ምልክትም ሲያደርግ ሊያይ ተስፋ ያደርግ ነበር። በብዙ ቃልም ጠየቀው፤ እርሱ ግን አንድ ስንኳ አልመለሰለትም። የካህናት አለቆችና ጻፎችም አጽንተው ሲከሱት ቆመው ነበር። ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር ናቀው ዘበተበትም፥ የጌጥ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው። ሄሮድስና ጲላጦስም በዚያን ቀን እርስ በርሳቸው ወዳጆች ሆኑ፥ ቀድሞ በመካከላቸው ጥል ነበረና። ጲላጦስም፥ የካህናትን አለቆችና መኳንንትን ሕዝቡንም በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ ሕዝቡን ያጣምማል ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እነሆም፥ በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል ስንኳ በዚህ ሰው አላገኘሁበትም። ሄሮድስም ደግሞ ምንም አላገኘም፤ ወደ እኛ መልሶታልና፤ እነሆም፥ ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም፤ እንግዲያስ ቀጥቼ እፈታዋለሁ። በበዓሉ አንድ ይፈታላቸው ዘንድ ግድ ነበረና። ሁላቸውም በአንድነት፦ ይህን አስወግድ፥ በርባንንም ፍታልን እያሉ ጮኹ፤ እርሱም ሁከትን በከተማ አንሥቶ ሰውን ስለ ገደለ በወኅኒ ታስሮ ነበር። ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታ ወድዶ ዳግመኛ ተናገራቸው፤ ነገር ግን እነርሱ፦ ስቀለው ስቀለው እያሉ ይጮኹ ነበር። ሦስተኛም፦ ምን ነው? ያደረገውስ ክፋት ምንድር ነው? ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ አላቸው። እነርሱ ግን እንዲሰቀል በታላቅ ድምፅ አጽንተው ለመኑት። የእነርሱ ጩኸትና የካህናት አለቆችም ቃል በረታ። ጲላጦስም ልመናቸው እንዲሆንላቸው ፈረደበት። ያንን የለመኑትንም፥ ስለ ሁከት ሰውንም ስለ መግደል በወኅኒ ታስሮ የነበረውን አስፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጠው።