በዚያ የተሰበሰቡት በሙሉ ተነሥተው ኢየሱስን ወደ ጲላጦስ ወሰዱት፤ እንዲህም እያሉ ይከስሱት ጀመር፤ “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያስት፣ ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ሲከለክል፣ ደግሞም፣ ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ’ ሲል አገኘነው።” ጲላጦስም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አንተው አልህ” አለው። ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ፣ “እኔ በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም” አለ። እነርሱ ግን፣ “ይህ ሰው ከገሊላ ጀምሮ እዚህ ድረስ መላውን ይሁዳ ሳይቀር እያወከ ነው” እያሉ አጽንተው ተናገሩ። ጲላጦስም ይህን ሲሰማ፣ ሰውየው የገሊላ ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ጠየቀ፤ ኢየሱስ ከሄድሮስ ግዛት የመጣ መሆኑን ጲላጦስ ባወቀ ጊዜ፣ ሄሮድስ በዚያን ወቅት በኢየሩሳሌም ስለ ነበረ ወደ እርሱ ላከው። ሄሮድስም ኢየሱስን ብዙ ጊዜ ሊያየው ይፈልግ ስለ ነበር፣ ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ ታምራት ሲሠራ ለማየት ተስፋ ያደርግ ነበር። ብዙ ጥያቄዎችንም አቀረበለት፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰለትም። የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም እዚያው ቆመው በብርቱ ይወነጅሉት ነበር። ሄሮድስም ከወታደሮቹ ጋር ናቀው፤ አፌዙበትም፤ የክብር ልብስ አልብሶም ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው። ሄሮድስና ጲላጦስም በዚሁ ዕለት ተወዳጁ፤ ቀደም ሲል ግን በመካከላቸው ጥል ነበረ። ጲላጦስም የካህናት አለቆችን፣ ገዥዎችንና ሕዝቡን በአንድነት ሰብስቦ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ሰው ሕዝቡን ለዐመፅ ያነሣሣል ብላችሁ ወደ እኔ አምጥታችሁት ነበር፤ እኔም በእናንተው ፊት መርምሬው፣ ባቀረባችሁበት ክስ አንዳች ወንጀል አላገኘሁበትም። ደግሞም ሄሮድስ እንዲሁ ምንም ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶታል፤ እንደምታዩት ይህ ሰው ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አልፈጸመም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።” ይህን ያለው በበዓሉ አንድ እስረኛ እንዲፈታላቸው የግድ ያስፈልግ ስለ ነበረ ነው። ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ላይ፣ “ይህን ሰው ወዲያ አስወግደው! በርባንን ፍታልን!” እያሉ ጮኹ፤ በርባንም በከተማ ውስጥ የሕዝብ ዐመፅ በማነሣሣትና በነፍስ ግድያ የታሰረ ሰው ነበር። ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታው ስለ ፈለገ፣ እንደ ገና ተናገራቸው፤ እነርሱ ግን፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ጲላጦስም ሦስተኛ ጊዜ፣ “ለምን? ይህ ሰው ምን የፈጸመው ወንጀል አለ? እኔ ለሞት የሚያበቃ ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ” አላቸው። እነርሱ ግን ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲሰቀል አጥብቀው ለመኑት፤ ጩኸታቸውም በረታ። ስለዚህ ጲላጦስ የጠየቁት እንዲፈጸም ውሳኔ አስተላለፈ። የሕዝብ ዐመፅ በማነሣሣትና በነፍስ ግድያ ታስሮ የነበረውን፣ እንዲፈታላቸውም የለመኑትን ያን ሰው ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን እንዳሻቸው እንዲያደርጉት አሳልፎ ሰጣቸው።
ሉቃስ 23 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 23
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 23:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos