ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለ ጠጎችን አየ። አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ። አንዳንዶቹም ስለ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ፦ ይህማ የምታዩት ሁሉ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል አለ። እነርሱም፦ መምህር ሆይ፥ እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ይሆን ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት። እንዲህም አለ፦ እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፦ እኔ ነኝ፥ ዘመኑም ቀርቦአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ። ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም። በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል። ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል። ሰለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።
የሉቃስ ወንጌል 21 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 21:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች