ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች መባቸውን በምጽዋት መቀበያ ሣጥን ውስጥ ሲጨምሩ አየ። እንዲሁም አንዲት ድኻ መበለት፥ ሁለት ሳንቲም የሚያኽል የናስ ገንዘብ በሣጥኑ ውስጥ ስትጨምር አየ። እንዲህም አለ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት፥ ከሁሉም አብልጣ ሰጥታለች። እነርሱ የሰጡት ከሀብታቸው የተረፋቸውን ነው፤ እርስዋ ግን ድኻ ሆና ሳለች ምንም ሳታስቀር ያላትን ሁሉ ሰጠች።” አንዳንድ ሰዎች፥ “ይህ ቤተ መቅደስ እንዴት ውብ ነው? በከበሩ ድንጋዮችና ለእግዚአብሔር በቀረቡ ስጦታዎች አጊጦአል” እያሉ ይነጋገሩ ነበር። ኢየሱስ ግን “ይህ የምታዩት ሁሉ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ የማይቀርበት ጊዜ ይመጣል፤ እነዚህ ድንጋዮች ሁሉ አንድ ቀን ይፈራርሳሉ።” እነርሱም “መምህር ሆይ! ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ይህስ የሚሆንበት ጊዜ መቃረቡን የምናውቅበት ምልክት ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እንዳትሳሳቱ ተጠንቀቁ! ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ! እነሆ፥ ጊዜው ቀርቦአል!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እነርሱን አትከተሉአቸው። ስለ ጦርነትና ስለ ሁከት በምትሰሙበት ጊዜም አትደንግጡ፤ አስቀድሞ ይህ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ይሁን እንጂ ፍጻሜው ወዲያውኑ አይሆንም።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል። በየቦታውም ብርቱ የምድር መናወጥ፥ ራብና ወረርሽኝ ይሆናል። የሚያስፈሩ ነገሮችና ታላላቅ ምልክቶች በሰማይ ላይ ይታያሉ። ነገር ግን ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ሰዎች እናንተን ይይዙአችኋል፤ ያሳድዱአችኋል፤ ወደ ምኲራብና ወደ ወህኒ ቤትም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ስለ ስሜም ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎች ይወስዱአችኋል። ይህም ስለ ስሜ ለመመስከር መልካም አጋጣሚ ይሆንላችኋል። ስለዚህ በሚቀርብባችሁ ክስ ስለምትሰጡት መልስ መጨነቅ እንደማይገባችሁ አስቀድማችሁ ልብ አድርጉ። ከጠላቶቻችሁ ማንም ሊቋቋመው ወይም ሊቃወመው የማይችለውን አንደበትና ጥበብ እኔ እሰጣችኋለሁ። ወላጆቻችሁና ወንድሞቻችሁ፥ ዘመዶቻችሁና ወዳጆቻችሁም ሳይቀሩ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ከእናንተ አንዳንዶቹ ይገደላሉ። ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ነገር ግን ከራሳችሁ ጠጒር አንዲት እንኳ አትጠፋም። በትዕግሥታችሁ ነፍሳችሁን ታድናላችሁ” አለ።
የሉቃስ ወንጌል 21 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 21:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች