ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው። ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር። እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። ጴጥሮስም፦ ጌታ ሆይ፥ ይህን ምሳሌ ለእኛ ወይስ ደግሞ ለሁሉ ትናገራለህን? አለው። ጌታም አለ፦ እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው። እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ባሪያ ግን፦ ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፥ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል። የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ፥ አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ? ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፥ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ? በምድር ላይ ሰላምንም ለመስጠት የመጣሁ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፥ መለያየትን እንጂ። ከአሁን ጀምሮ በአንዲት ቤት አምስት ሰዎች ይኖራሉና፤ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ሁለቱም በሦስቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። አባት በልጁ ላይ ልጅም በአባቱ ላይ፥ እናት በልጅዋ ላይ ልጅዋም በእናትዋ ላይ፥ አማት በምራትዋ ላይ ምራትም በአማትዋ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። ደግሞም ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፥ ወዲያው፦ ዝናብ ይመጣል ትላላችሁ፥ እንዲሁም ይሆናል፤ በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ፦ ትኩሳት ይሆናል ትላላችሁ፥ ይሆንማል። እናንት ግብዞች፥ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፥ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው? ራሳችሁ ደግሞ ጽድቅን የማትፈርዱ ስለ ምን ነው? ከባላጋራህ ጋር ወደ ሹም ብትሄድ፥ ወደ ዳኛ እንዳይጐትትህ ዳኛውም ለሎሌው አሳልፎ እንዳይሰጥህ ሎሌውም በወኅኒ እንዳይጥልህ፥ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ እንድትታረቅ ትጋ። እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ግማሽ ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ ከቶ አትወጣም።
የሉቃስ ወንጌል 12 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 12:35-59
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች