ሉቃስ 12:35-59

ሉቃስ 12:35-59 NASV

“በዐጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ ጌታቸው ከሰርግ ግብዣ እስኪመለስ የሚጠባበቁና መጥቶም በር ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችን ምሰሉ። ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው ባሮች ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በዐጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል። ከሌሊቱ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንደዚያው ነቅተው ቢያገኛቸው፣ እነዚያ ባሮች ብፁዓን ናቸው። ይህን ግን ዕወቁ፤ ሌባ በምን ሰዓት እንደሚመጣ ባለቤቱ ቢያውቅ ኖሮ፣ ቤቱ ሲቈፈር ዝም ብሎ ባላየ ነበር። የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣል፤ እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ።” ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ብቻ ነው ወይስ ለሁሉም ጭምር ነው?” አለው። ጌታም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እንግዲህ፣ ምግባቸውን በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው፣ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልኅ መጋቢ ማነው? ጌታው ሲመለስ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ባሪያ እርሱ ምስጉን ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ነገር ግን ያ ባሪያ፣ ‘ጌታዬ ቶሎ አይመጣም፤ ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብና ወንድና ሴት ብላቴኖችን ቢደበድብ፣ ደግሞም እንዳሻው ቢበላና ቢጠጣ መስከር ቢጀምር፣ የዚያ ባሪያ ጌታ ባላሰበው ቀንና ባልጠረጠረው ሰዓት ይመጣበታል፤ ስለዚህ ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከማያምኑ ጋራ ያደርጋል። “የጌታውን ፍላጎት እያወቀ የማይዘጋጅና ፈቃዱን የማያደርግ ባሪያ እርሱ ክፉኛ ይገረፋል፤ ነገር ግን ይህን ሳያውቅ ቀርቶ መገረፍ የሚገባውን ያህል ያደረገ አገልጋይ በጥቂቱ ይገረፋል። ብዙ ከተሰጠው ሁሉ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራ ከተቀበለም ብዙ ይጠበቅበታል። “እኔ የመጣሁት በምድር ላይ እሳት ለመለኰስ ነው፤ አሁኑኑ ቢቀጣጠል ምንኛ ደስ ባለኝ! ነገር ግን የምጠመቀው ጥምቀት አለኝ፤ እስኪፈጸምም ድረስ እንዴት ተጨንቄአለሁ? በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ ይመስላችኋል? አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እኔ የመጣሁት ለመለያየት ነው። ከአሁን ጀምሮ እርስ በርስ የተለያዩ በአንድ ቤተ ሰብ ውስጥ ዐምስት ሰዎች ይኖራሉ፤ ሁለቱ በሦስቱ ላይ፣ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። አባት በወንድ ልጁ ላይ፣ ወንድ ልጅም በአባቱ ላይ፣ እናት በሴት ልጇ ላይ፣ ሴት ልጅም በእናቷ ላይ፣ ዐማት በምራቷ ላይ፣ ምራትም በዐማቷ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ።” ደግሞም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ደመና በምዕራብ በኩል ሲወጣ ስታዩ ወዲያው፣ ‘ዝናብ ሊመጣ ነው’ ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል፤ የደቡብ ነፋስም ከደቡብ በኩል ሲነፍስ፣ ‘ቀኑ ሞቃት ይሆናል’ ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል። እናንተ ግብዞች፤ የምድሩንና የሰማዩን መልክ መመርመር ታውቁበታላችሁ፤ ታዲያ ይህን የአሁኑን ዘመን መመርመር እንዴት ተሳናችሁ? “ታዲያ ራሳችሁ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለምን አትፈርዱም? ከባላጋራህ ጋራ ወደ ዳኛ ፊት ለመቅረብ ስትሄድ፣ ገና በመንገድ ላይ ሳለህ ለመታረቅ ጥረት አድርግ፤ አለዚያ ጐትቶ ወደ ዳኛው ይወስድሃል፤ ዳኛውም ለመኰንኑ አሳልፎ ይሰጥሃል፤ መኰንኑም ወደ ወህኒ ይጥልሃል። እልሃለሁ፤ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።”