የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 7

7
1የበደል መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 2የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት ስፍራ የበደሉን መሥዋዕት ያርዱታል፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጨዋል። 3ስቡንም ሁሉ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ያቀርበዋል። 4ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ይወስዳል። 5ካህኑም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱ የበደል መሥዋዕት ነው። 6ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤ በተቀደሰ ስፍራ ይበሉታል፤ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 7የኃጢአት መሥዋዕት እንደ ሆነ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ለሁለቱ አንድ ሕግ ነው፤ በእርሱ የሚያስተሰርይ ካህን ይወስደዋል። 8የማናቸውንም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ካህን ያቀረበው የሚቃጠለው መሥዋዕት ቁርበት ለዚያው ካህን ይሆናል። 9በእቶን የተጋገረው የእህል ቍርባን ሁሉ፥ በመቀቀያም ወይም በምጣድ የበሰለው ሁሉ ለሚያቀርበው ካህን ይሆናል። 10በዘይትም የተለወሰው ወይም የደረቀው የእህል ቍርባን ሁሉ ለአሮን ልጆች ሁሉ ይሆናል፤ ለሁሉም ይሆናል። 11ሰው ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ነው። 12ለምስጋና ቢያቀርበው፥ ከምስጋናው መሥዋዕት ጋር በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ በዘይትም የተለወሰ መልካም ዱቄት ያቀርባል። 13ለምስጋና የሚሆነውን የደኅንነት መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ እርሾ ያለበትን ኅብስት ያቀርባል። 14ከቍርባኑም ሁሉ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን እንዲሆን ከእነርሱ አንዱን ያነሣል። እርሱም የደኅንነትን መሥዋዕት ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል። 15ለምስጋና የሚሆነው የደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ በሚቀርብበት ቀን ይበሉታል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አያድርም። 16የቁርባኑም መሥዋዕት የስእለት ወይም የፈቃድ ቢሆን፥ መሥዋዕቱ በሚቀርብበት ቀን ይብሉት፤ ከእርሱም የቀረውን በነጋው ይብሉት፤ 17ከመሥዋዕቱም ሥጋ እስከ ሦስተኛው ቀን የሚቆየው በእሳት ይቃጠላል። 18በሦስተኛው ቀን ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ አይሠምርም ላቀረበው ሰው የተጠላ ይሆንበታል እንጂ ቁርባን ሆኖ አይቈጠርለትም፤ ከእርሱም ቢበላ ኃጢአቱን ይሸከማል። 19ርኩስ ነገር የሚነካውን ሥጋ አይብሉት፤ በእሳት ይቃጠል። ንጹሕ የሆነ ሰው ሁሉ ግን ከሥጋው ይብላ። 20ሰውም የረከሰ ቢሆን፥ ለእግዚአብሔርም ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 21ማናቸውንም ርኩስ ነገር ቢነካ፥ የሰውን ወይም የረከሰን እንስሳ ወይም ሌላውን የተጠላ ርኩስን ቢነካ፥ ለእግዚአብሔርም ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 22እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 23የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ የበሬ ወይም የበግ ወይም የፍየል ስብ ከቶ አትብሉ። 24የሞተውን ስብ፥ አውሬ የሰበረውንም ስብ ለሌላ ተግባር አድርጉት፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም አትብሉ፤ 25ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ከእንስሳ ስብ የሚበላ ሁሉ፥ ያ የበላ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና። 26በማደሪያዎቻችሁም ሁሉ የወፍ ወይም የእንስሳ ደም ቢሆን አትብሉ። 27ደም የሚበላ ሰው ሁሉ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። 28እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 29የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ ለእግዚአብሔር የደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ቁርባኑን ለእግዚአብሔር ከደኅንነቱ መሥዋዕት ያመጣል። 30የእርሱ እጆች ለእግዚአብሔር የእሳቱን ቁርባን ያመጣሉ፤ ፍርምባው በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ይወዘውዝ ዘንድ ስቡንና ፍርምባውን ያመጣል። 31ካህኑም ስቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል፤ ፍርምባውም ለአሮንና ለልጆቹ ይሁን። 32ከደኅንነት መሥዋዕታችሁ ቀኝ ወርቹን ለማንሣት ቁርባን እንዲሆን ለካህኑ ትሰጡታላችሁ። 33ከአሮንም ልጆች የደኅንነትን መሥዋዕት ደሙንና ስቡን ለሚያቀርብ ለእርሱ ቀኝ ወርቹ እድል ፈንታው ይሆናል። 34የሚወዘወዘውን ፍርምባና የሚነሣውን ወርች ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕታቸው ወስጄአለሁ፥ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ለዘላለም እድል ፈንታ እንዲሆን ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ሰጥቼአቸዋለሁ። 35እግዚአብሔርን በክህነት ያገለግሉት ዘንድ ባቀረባቸው ቀን ለእግዚአብሔር ከሆነ ከእሳት ቁርባን የአሮንና የልጆቹ እድል ፈንታ ይህ ነው። 36ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም እድል ፈንታቸው እንዲሆን በቀባቸው ቀን የእስራኤል ልጆች ይሰጡአቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው። 37የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቁርባን፥ የኃጢአትና የበደል መሥዋዕት፥ የቅድስናና የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። 38እግዚአብሔር በሲና ምድረ በዳ ቁርባናቸውን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ባዘዘ ጊዜ በሲና ተራራ ለሙሴ ያዘዘው ይህ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ