የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 6

6
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2ማናቸውም ሰው ኃጢአትን ቢሠራ፥ እግዚአብሔርንም ቢበድል፥ ያኖረበትን አደራ ወይም ብድር ወስዶ ባልንጀራውን ቢክድ፥ ወይም ቢቀማ፥ ወይም በባልንጀራው ላይ ግፍ ቢያደርግ፥ 3ወይም የጠፋውን ነገር ቢያገኝ፥ ያንንም ሸሽጎ በሐሰት ቢምል፥ ሰው ከሚያደርጋቸው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንዲቱ ቢበድል፥ 4እርሱ ኃጢአትን ሠርቶ በደለኛ ቢሆን፥ በቅሚያ የወሰደውን ወይም በግፍ የተቀበለውን ወይም የተሰጠውን አደራ ወይም ጠፍቶ ያገኘውን፥ 5ወይም በሐሰት የማለበትን ነገር ይመልስ፤ በሙሉ ይመልስ፥ ከዚያም በላይ አምስተኛውን ክፍል ጨምሮ የበደሉን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ቀን ለባለ ገንዘቡ ይስጠው። 6ስለ በደል መሥዋዕትም ለእግዚአብሔር ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ እንደ ግምጋሜህ መጠን ስለ በደል መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያምጣ። 7ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ስለዚያም ስላደረገው በደል ሁሉ ይቅር ይባላል። 8እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 9አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ የሚቃጠለው የመሥዋዕቱ ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ባለው እንጨት ላይ ሌሊቱን ሁሉ እስኪጸባ ድረስ ይሆናል፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል። 10ካህኑም የበፍታ ቀሚስና የበፍታ ሱሪ በሥጋው ላይ ይለብሳል፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳቱ ከበላው በኋላ አመዱን አንሥቶ በመሠዊያው አጠገብ ያፈስሰዋል። 11ልብሱንም ያወልቃል፥ ሌላም ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ተሸክሞ ከሰፈሩ ንጹሕ ስፍራ ወደ ሆነ ወደ ውጭ ያወጣዋል። 12እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል፥ አይጠፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ እንጨት ያቃጥለበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ በዚያም የደኅንነትን መሥዋዕት ስብ ያቃጥላል። 13ዘወትር በመሠዊያው ላይ እሳት ይነድዳል፤ አይጠፋም። 14የእህሉም ቍርባን ሕግ ይህ ነው፤ የአሮን ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በመሠዊያው ፊት ያቀርቡታል። 15ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መልካሙን ዱቄት ከዘይት ጋር እፍኝ ሙሉ፥ ደግሞም በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውን ዕጣን ሁሉ ያነሣል፥ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 16ከእርሱም የተረፈውን አሮንና ልጆቹ ይበሉታል፤ ቂጣ ሆኖ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ ይበሉታል። 17በእርሾ ቦክቶ አይጋገርም። እርሱን ከእሳቱ ቍርባኔ ለእነርሱ እድል ፈንታ እንዲሆን ሰጠሁ፤ እርሱም እንደ ኃጢአትና እንደ በደል መሥዋዕት ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 18ለእግዚአብሔር ከቀረበ ከእሳት ቍርባን ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ እድል ፈንታቸው እንዲሆን ከአሮን ልጆች ወንዶቹ ሁሉ ይበሉታል። የሚነካቸው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 19እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 20በተቀቡበት ቀን የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል መልካሙን ዱቄት እኵሌታውን በጥዋት፥ እኵሌታውንም በማታ ለዘወትር የእህል ቍርባን አድርገው ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የአሮንና የልጆቹ ቍርባን ይህ ነው። 21ከዘይት ጋር በምጣድ ላይ ይደረጋል፤ ሲለወስ ታገባዋለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የእህሉን ቍርባን ቈራርሰህ ታቀርበዋለህ። 22ከልጆቹም በአባቱ ፋንታ የተቀባው ካህን ያቀርበዋል። ለዘላለም ሥርዓት እንዲሆን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር ይቃጠላል። 23ካህኑም የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠላል፤ ከእርሱም አንዳች አይበላም። 24እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 25አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ የኃጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአቱ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል፤ እርሱ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 26ለኃጢአት የሚሠዋው ካህን ይበላዋል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል። 27ሥጋውን የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፤ ማናቸው ልብስ ደም ቢረጭበት የተረጨበትን በተቀደሰ ስፍራ ታጥበዋለህ። 28የሚቀቀልበትም ሸክላ ይሰበራል፤ በናስም ዕቃ ቢቀቀል ይፈገፈጋል፥ በውኃም ይለቀለቃል። 29ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከእርሱ ይበላል፤ እርሱ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 30ነገር ግን በመቅደሱ ውስጥ ለማስተስረያ ይሆን ዘንድ ከደሙ ወደ መገናኛው ድንኳን የሚገባው የኃጢአት መሥዋዕት ሁሉ አይበላም፤ በእሳት ይቃጠላል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ