ኦሪት ዘሌዋውያን 5
5
1ማንም ሰው የሚያምለውን ቃል ቢሰማ፥ ምስክር ሆኖም አንድ ነገር አይቶ እንደ ሆነ ወይም አውቆ እንደ ሆነ ባይናገር፥ ኃጢአት መሥራቱ ነውና በደሉን ይሸከማል። 2ማናቸውም ሰው ሳይታወቀው ርኩስ ነገር ቢነካ፥ የረከሰም አውሬ በድን፥ ወይም የረከሰ ከብት በድን፥ ወይም የረከሰ የተንቀሳቀሰ እንስሳ በድን ቢሆን፥ እርሱም ርኩስ ቢሆን ነገሩ በታወቀው ጊዜ በደል ይሆንበታል፤ 3ወይም ርኩስነቱን ሳያውቅ ርኩስን ሰው ቢነካ፥ በማናቸውም ርኩሰት ቢረክስ፥ ነገሩ በታወቀው ጊዜ በደል ይሆንበታል። 4ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ክፉን ወይም መልካምን ያደርግ ዘንድ ሳያስብ በከንፈሩ ተናግሮ ቢምል፤ ሳያስብ የማለው ስለ ማናቸውም ነገር ቢሆን፤ በታወቀው ጊዜ ከዚህ ነገር በአንዱ በደለኛ ይሆናል። 5ከእነዚህ ነገሮች በአንዲቱ በደለኛ ሲሆን፥ የሠራውን ኃጢአት ይናዘዛል። 6ስለ ሠራው ኃጢአት ለእግዚአብሔር የበደል መሥዋዕት ያመጣል፤ እርሱም ከመንጋው የበግ ወይም የፍየል እንስት ለኃጢአት መሥዋዕት ይሆናል፤ ካህኑም ስለ ኃጢአቱ ያስተሰርይለታል። 7ስለ ሠራው ኃጢአት ለበደል መሥዋዕት ጠቦትን ለማምጣት ገንዘቡ ያልበቃ እንደ ሆነ፥ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእግዚአብሔር ያቀርባል። 8ወደ ካህኑም ያመጣቸዋል፤ እርሱም አስቀድሞ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ያቀርባል፥ ራሱንም ከአንገቱ ይቈለምመዋል፥ ነገር ግን አይቈርጠውም። 9ከኃጢአቱም መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ግድግዳ ላይ ይረጨዋል፤ የተረፈውም ደም ከመሠዊያው በታች ይንጠፈጠፋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 10እንደ ሥርዓቱም ሁለተኛውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያዘጋጀዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 11ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ለማምጣት ገንዘቡ ያልበቃ እንደ ሆነ፥ ስለ ሠራው ኃጢአት የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል መልካም ዱቄት ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነውና ዘይት አያፈስስበትም፥ ዕጣንም አይጨምርበትም። 12ወደ ካህኑም ያመጣዋል፥ ካህኑም መታሰቢያው ይሆን ዘንድ ከእርሱ እፍኝ ሙሉ ይውሰድ፥ ለእግዚአብሔርም በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱም የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 13ካህኑም ከእነዚያ በአንዳቸው ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። የተረፈውም እንደ እህል ቍርባን ለካህኑ ይሆናል። 14እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 15ማናቸውም ሰው ቢበድል፥ ሳያውቅም ለእግዚአብሔር በተቀደሰው በማናቸውም ነገር ኃጢአትን ቢሠራ፥ ለበደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከመንጋ ነውር የሌለበትን አውራ በግ ያቀርባል፤ እንደ ግምጋሜህ መጠን በብር ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ለበደል መሥዋዕት ያቀርበዋል። 16በተቀደሰ ነገር ላይ ስለ ሠራው ኃጢአት ዕዳ ይከፍላል፥ አምስተኛውንም እጅ ይጨምርበታል፥ ለካህኑም ይሰጠዋል። ካህኑም በበደል መሥዋዕት አውራ በግ ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 17ማናቸውም ሰው ኃጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ ባያውቅም፥ ያ ሰው በደለኛ ነው፥ ኃጢአቱንም ይሸከማል። 18ነውር የሌለበትን አውራ በግ ከመንጋው ለበደል መሥዋዕት እንደ ግምጋሜህ መጠን ወደ ካህኑ ያመጣዋል፤ ካህኑም ሳያውቅ ስለ ሳተው ስሕተት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 19እርሱም የበደል መሥዋዕት ነው፤ በእውነት በእግዚአብሔር ፊት በደለኛ ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 5: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ