እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለእናንተ ጣዖት አታድርጉ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ። ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። በሥርዓቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም፥ ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቍረጥ ይደርሳል፥ የወይኑም መቍረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በጸጥታ ትኖራላችሁ። በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ። ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም አሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። ፊቴም ወደ እናንተ ይሆናል፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። ብዙ ጊዜ የተቀመጠውንም አሮጌውን እህል ትበላላችሁ፤ ከአዲሱም በፊት አሮጌውን ታወጣላችሁ። ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁም እሄዳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። ባሪያዎች እዳትሆኑአቸው ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ። ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ ሥርዓቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ነፍሳችሁ ፍርዴን ብትጸየፍ፥ እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ክሳትንም፥ ዓይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያማስን ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፥ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። ጕልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም እህልዋን አትሰጥም፥ የምድርም ዛፎች ፍሬአቸውን አይሰጡም። በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ ባትሰሙኝም፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። በመካከላችሁም የምድርን አራዊት እሰድዳለሁ፤ ልጆቻችሁንም ይነጥቃሉ፥ እንሰሶቻችሁንም ያጠፋሉ፥ እናንተንም ያሳንሳሉ፤ መንገዶቻችሁም በረሃ ይሆናሉ። እስከዚህም ድረስ ባትቀጡ፥ በእንቢተኝነትም ብትሄዱ፥ እኔ ደግሞ በእንቢተኝነት እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። የቃል ኪዳኔንም በቀል ይበቀልባችሁ ዘንድ ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተማችሁም ትሰበሰባላችሁ፥ ቸነፈርንም እሰድድባችኋለሁ፤ በጠላትም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ። የእህላችሁንም ድጋፍ በሰበርሁ ጊዜ፥ አሥር ሴቶች እንጀራቸውን በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፥ በሚዛንም መዝነው እንጀራችሁን ይመልሱላችኋል፤ በበላችሁም ጊዜ አትጠግቡም።
ኦሪት ዘሌዋውያን 26 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 26:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች