የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 20

20
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2ደግሞ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ከእስራኤል ልጆች ወይም በእስራኤል ዘንድ ከሚቀመጡ እንግዶች ማናቸውም ሰው ዘሩን ለሞሎክ ቢሰጥ ፈጽሞ ይገደል፤ የአገሩ ሕዝብ በድንጋይ ይውገረው። 3መቅደሴን ያረክስ ዘንድ፥ የተቀደሰውንም ስሜን ያጐሰቁል ዘንድ ዘሩን ለሞሎክ ሰጥቶአልና እኔ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፥ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 4ዘሩንም ለሞሎክ ሲሰጥ፥ የአገሩ ሕዝብ ያን ቸል ቢለው ባይገድሉትም፥ 5እኔ በዚያ ሰውና በቤተሰቡ ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፤ እርሱንም፥ ከሞሎክም ጋር ያመነዝሩ ዘንድ የሚከተሉትን ሁሉ ከሕዝባቸው መካከል ለይቼ አጠፋለሁ። 6መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቍዮችንም በሚከተል፥ በሥራቸውም በሚያመነዝር፥ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፥ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 7እንግዲህ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ። 8ሥርዓቴን ጠብቁ፥ አድርጉትም፤ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ነኝ። 9ማናቸውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን ቢሰድብ ፈጽሞ ይገደል፥ አባቱንና እናቱን ሰድቦአልና፤ ደሙ በራሱ ላይ ነው። 10ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ወይም ከባልጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር አመንዝራውና አመንዝራይቱ ፈጽመው ይገደሉ። 11ማናቸውም ሰው ከአባቱ ሚስት ጋር ቢተኛ የአባቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ሁለቱ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው። 12ማናቸውም ሰው ከምራቱ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ፈጽመው ይገደሉ፤ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ደማቸውም በላያቸው ነው። 13ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው። 14ማናቸውም ሰው እናቲቱንና ልጂቱን ቢያገባ ርኵሰት ነው፤ በመካከላችሁ ኃጢአት እንዳይሆን እርሱና እነርሱ በእሳት ይቃጠሉ። 15ማናቸውም ሰው ከእንስሳ ጋር ቢገናኝ ፈጽሞ ይገደል፤ እንስሳይቱንም ግደሉአት። 16ማናቸይቱም ሴት ወደ እንስሳ ብትቀርብ፥ ከእነርሱም ጋር ብትገናኝ፥ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው። 17ማናቸውም ሰው የአባቱን ልጅ ወይም የእናቱን ልጅ እኅቱን ቢያገባ፥ ኃፍረተ ሥጋዋንም ቢያይ፥ ኃፍረተ ሥጋውንም ብታይ፥ ይህ ጸያፍ ነገር ነው፤ በሕዝባቸውም ልጆች ፊት ይገደሉ፤ የእኅቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአልና ኃጢአቱን ይሸከማል። 18ማናቸውም ሰው ከባለ መርገም ሴት ጋር ቢተኛ ኃፍረተ ሥጋዋንም ቢገልጥ፥ ፈሳሽዋን ገልጦአልና፥ እርስዋም የደምዋን ፈሳሽ ገልጣለችና ሁለቱ ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ። 19የአባትህን ወይም የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ ይህን የሚያደርግ የዘመድን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ። 20ሰውም ከአጎቱ ሚስት ጋር ቢተኛ፥ የአጎቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ፤ ያለ ልጅ ይሞታሉ። 21ሰውም የወንድሙን ሚስት ቢያገባ ርኵሰት ነው፤ የወንድሙን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ያለ ልጅ ይሆናሉ። 22እንግዲህ ትቀመጡባት ዘንድ የማገባችሁ ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዓቴን ሁሉ፥ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ፥ አድርጉትም። 23ከፊታችሁ በምጥላቸውም ሕዝብ ወግ አትሂዱ፤ ይህን ሁሉ አድርገዋልና ተጸየፍኋቸው። 24ነገር ግን እናንተን፦ ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ትወርሱአትም ዘንድ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣችኋለሁ አልኋችሁ። እኔ ከአሕዛብ የለየኋችሁ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ። 25እንግዲህ ንጹሑን እንስሳ ከርኩሱ፥ ንጹሑንም ወፍ ከርኩስ ትለያላችሁ፤ ርኩሶች ናቸው ብዬ በለየኋቸው በእንስሳና በወፍ በምድርም ተንቀሳቃሽ ሁሉ ነፍሳችሁን አታርክሱ። 26እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፥ ለእኔም ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁና ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ። 27ሰው ወይም ሴት መናፍስት ቢጠሩ ወይም ጠንቍዮች ቢሆኑ ፈጸመው ይገደሉ፤ በድንጋይ ይውገሩአቸው፤ ደማቸው በላያቸው ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ