የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 22

22
1ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ፦
2በውኑ ሰው እግዚአብሔርን ይጠቅመዋልን?
በእውነት ጥበበኛ ሰው ራሱን ይጠቅማል።
3ጻድቅ መሆንህስ ሁሉን የሚችለውን አምላክ ደስ ያሰኘዋልን?
መንገድህን ማቅናትህስ ይጠቅመዋልን?
4እርሱንስ ስለ ፈራህ ይዘልፍሃልን?
ወደ ፍርድስ ከአንተ ጋር ይገባልን?
5ክፋትህስ የበዛ አይደለምን?
ለኃጢአትህም ፍጻሜ የላትም።
6የወንድሞችህን መያዣ በከንቱ ወስደሃል፥
የእርዘኞቹንም ልብስ ዘርፈሃል።
7ለደካማ ውኃ አላጠጣህም፥
ለራብተኛም እንጀራን ከልክለሃል።
8በክንድ የበረታ ምድርን ገዛ፥
ከበርቴውም ሰው ተቀመጠባት።
9መበለቲቱን አንዳች አልባ ሰድደሃታል፥
የድሀ አደጎችም ክንድ ተሰብሮአል።
10ስለዚህ አሽክላ ከብቦሃል፥
ድንገተኛ ፍርሃትም አናውጦሃል።
11እንዳታይ ብርሃን ጨለማ ሆነችብህ፥
የውኆችም ብዛት አሰጠመህ።
12እግዚአብሔር በሰማያት ከፍ ከፍ አይልምን?
ከዋክብትም እንዴት ከፍ ከፍ እንዳሉ ተመልከት።
13አንተም፦ እግዚአብሔር ምን ያውቃል?
በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ሊፈርድ ይችላልን?
14እንዳያይ የጠቈረ ደመና ጋርዶታል፥
በሰማይ ክበብ ላይ ይራመዳል ብለሃል።
15በውኑ ኃጢአተኞች ሰዎች የረገጡአትን
የዱሮይቱን መንገድ ትጠብቃለህን?
16ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፥
መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ።
17እግዚአብሔርንም፦ ከእኛ ዘንድ ራቅ፥
ሁሉንም የሚችል አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል? አሉት።
18ነገር ግን ቤታቸውን በመልካም ነገር ሞላ፥
የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።
19ጻድቃን ያዩታል፥ ደስም ይላቸዋል፥
ንጹሐንም በንቀት ይስቁባቸዋል።
20በእውነት ሀብታቸው ጠፋ፥
የቀረውንም እሳት በላች።
21አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፥
በዚያም በጎነት ታገኛለህ።
22ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥
በልብህም ቃሉን አኑር፥
23ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥
ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥
24የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥
የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥
25ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል።
26የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥
ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ።
27ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፥
ስእለትህንም ትሰጣለህ።
28ነገርንም ትመክራለህ፥ እርሱም ይሳካልሃል፥
ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል።
29ቢያዋርዱህ አንተ ከፍ ከፍ ትላለህ፥
ትሑቱንም ሰው ያድነዋል።
30ንጹሑን ሰው ያድነዋል፥
በእጅህም ንጽሕና ትድናለህ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ