የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 21

21
1ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
2ስሙ፥ ቃሌን ስሙ፥
ይህም መጽናናታችሁ ይሁን።
3እናገር ዘንድ ተውኝ፥
ከተናገርሁም በኋላ ተሳለቁ።
4በውኑ የኅዘን እንጕርጕሮዬ ለሰው እናገራለሁን?
አለመታገሥ ስለ ምን አይገባኝም?
5ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ተደነቁም፥
እጃችሁንም በአፋችሁ ላይ አኑሩ።
6እኔ ባሰብሁ ቍጥር እጨነቃለሁ፥
ፃዕርም ሥጋዬን ይይዛል።
7ስለ ምን ኃጢአተኞች በሕይወት ይኖራሉ?
ስለ ምንስ ያረጃሉ? በባለጠግነትስ ስለ ምን ይበረታሉ?
8ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፥
ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው።
9ቤታቸው ከፍርሃት ወጥቶ የታመነ ነው፥
የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።
10ኮርማቸው ይወልዳል፥ ዘሩንም አይጥለውም፥
ላማቸውም ትወልዳለች፥ አትጨነግፍም።
11ሕፃናቶቻቸውን እንደ መንጋ ያወጣሉ፥
ልጆቻቸውም ይዘፍናሉ።
12ከበሮና መሰንቆ ወስደው ይዘምራሉ፥
በእምቢልታ ድምፅ ደስ ይላቸዋል።
13ዕድሜያቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ፥
ድንገትም ወደ ሲኦል ይወርዳሉ።
14እግዚአብሔርንም፦ ከእኛ ዘንድ ራቅ፥
መንገድህን እናውቅ ዘንድ አንወድድም።
15እናመልከውስ ዘንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ማን ነው?
ወይስ ወደ እርሱ ብንጸልይ ምን ይጠቅመናል? ይላሉ።
16እነሆ፥ ሀብታቸው በእጃቸው ውስጥ አይደለምን?
የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።
17የኃጥአን መብራት የጠፋው፥
መቅሠፍትም የመጣባቸው፥
እግዚአብሔርም በቍጣው መከራ የከፈላቸው፥
18በነፋስ ፊት እንደ ገለባ፥
ዐውሎ ነፋስም እንደሚወስደው ትቢያ የሆኑ ስንት ጊዜ ነው?
19እናንተ፦ እግዚአብሔር በደላቸውን ለልጆቻቸው ይጠብቃል ብላችኋል።
እነርሱ ያውቁ ዘንድ ፍዳን ለራሳቸው ይክፈል።
20ዓይኖቻቸው ጥፋታቸውን ይዩ፥
ሁሉን ከሚችል አምላክ ቍጣ ይጠጡ።
21የወራታቸውስ ቍጥር ቢቈረጥ፥
ከእነርሱ በኋላ የቤታቸው ደስታ ምን ይሆናቸዋል?
22ከፍ ከፍ ባሉትስ ላይ ለሚፈርድ ለእግዚአብሔር
በውኑ ሰው እውቀትን ያስተምራልን?
23አንድ ሰው በሰላም ተዘልሎ ሲቀመጥ
በሙሉ ኃይሉ ሳለ ይሞታል።
24በአንጀቱ ውስጥ ስብ ሞልቶአል፥
የአጥንቶቹም ቅልጥም ረጥቦአል።
25ሌላውም ሰው መልካምን ነገር ከቶ ሳይቀምስ
በተመረረች ነፍስ ይሞታል።
26በአፈር ውስጥ በአንድ ላይ ይተኛሉ፥
ትልም ይከድናቸዋል።
27እነሆ፥ አሳባችሁን፥
የመከራችሁብኝንም ክፉ ምክር አውቄዋለሁ።
28እናንተ፦ የከበርቴው ቤት የት ነው?
ኃጢአተኛውም ያደረበት ድንኳን የት ነው? ብላችኋል።
29መንገድ አላፊዎችን አልጠየቃችሁምን?
ምልክታቸውን አታውቁምን?
30ኃጢአተኛው በመቅሠፍት ቀን እንደ ተጠበቀ፥
በቍጣው ቀን እንደሚድን።
31መንገዱን በፊቱ የሚናገር ማን ነው?
የሠራውንስ የሚመልስበት ማን ነው?
32እርሱን ግን ወደ መቃብር ይሸከሙታል፥
ሰዎቹም በመቃብሩ ላይ ይጠብቃሉ።
33የሸለቆው ጓል ይጣፍጥለታል፥
በኋላውም ሰው ሁሉ ይሳባል፥
በፊቱም ቍጥር የሌለው ጉባኤ አለ።
34የምትመልሱልኝ ውስልትና ነውና
በከንቱ እንዴት ታጽናኑኛላችሁ?

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ