የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 27

27
1በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ። 2እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፦ እስራትና ቀንበር ሥራ በአንገትህም ላይ አድርግ፥ 3ወደ ይሁዳ ንጉሥም ወደ ሴዴቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት መልእክተኞች እጅ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ ወደ ሞዓብም ንጉሥ ወደ አሞንም ልጆች ንጉሥ ወደ ጢሮስም ንጉሥ ወደ ሲዶናም ንጉሥ ላካቸው። 4ለጌቶቻቸውም እንዲነግሩ እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለጌቶቻችሁ እንዲህ በሉ፦ 5ምድሪቱን በምድርም ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን በታላቅ ኃይሌና በተዘረጋችው ክንዴ ፈጥሬአለሁ፥ ለዓይኔም መልካም ለሆነው እሰጣታለሁ። 6አሁንም እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለባሪያዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ፥ ይገዙለትም ዘንድ የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ። 7የገዛ ራሱም ምድር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና ለልጅ ለልጅ ልጁም ይገዛሉ፥ በዚያን ጊዜም ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እርሱን ያስገዙታል። 8ለባቢሎን ንጉሥም ለናቡከደነፆር የማይገዛውን፥ ከባቢሎንም ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የማያደርገውን ሕዝብና መንግሥት፥ ያን ሕዝብ በእጁ እስካጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እቀጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 9እናንተ ግን፦ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን ነቢያቶቻችሁንና ምዋርተኞቻችሁን፥ ሕልም አላሚዎቻችሁንና ቃላተኞቻችሁን መተተኞቻችሁንም አትስሙ፥ 10ከምድራቸሁ እንዲያርቁአችሁ፥ እኔም እንዳሳድዳችሁ እናንተም እንድትጠፉ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና። 11ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚገዛለትን ሕዝብ በአገሩ ላይ እተወዋለሁ፥ እነርሱም ያርሱአታል ይቀመጡባትማል።
12ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም በዚህ ቃል ተናገርሁ፦ ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገታችሁን ዝቅ አድርጉ ለእርሱና ለሕዝቡም ተገዙላቸው በሕይወትም ኑሩ። 13ለባቢሎን ንጉሥ ይገዛ ዘንድ እንቢ ስላለ ሕዝብ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፥ አንተና ሕዝብህ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለምን ትሞታላችሁ? 14ሐሰተኛን ትንቢት ይናገሩላችኋልና፦ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ። 15እኔ አልላክኋቸውምና፥ ነገር ግን እኔ እንዳሳድዳችሁ፥ እናንተና ትንቢት የሚናገሩላችሁ ነቢያትም እንድትጠፉ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
16ለካህናትም ለዚህም ሕዝብ እንዲህ ብዬ ተናገርሁ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሐሰተኛውን ትንቢት ይናገሩላችኋልና፦ የእግዚአብሔር ቤት ዕቃ በቅርብ ጊዜ ከባቢሎን ይመለሳል የሚሉአችሁን የነቢያቶቻችሁን ቃል አትስሙ። 17እነርሱም አትስሙ፥ ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ በሕይወትም ኑሩ። ይህችስ ከተማ ስለ ምን ባድማ ትሆናለች? 18እነርሱ ግን ነቢያት ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በእነርሱ ዘንድ ቢገኝ፥ በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት በኢየሩሳሌምም የቀረችው ዕቃ ወደ ባቢሎን እንዳትሄድ ወደ ሠራዊት ጌታ ወደ እግዚአብሔር ይማለሉ። 19-20የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ከበርቴዎች ሁሉ ማርኮ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ባፈለሳቸው ጊዜ ስላልወሰዳቸው ዓምዶች ስለ ኵሬውም ስለ መቀመጫዎቹም በዚህችም ከተማ ስለ ቀረች ዕቃ ሁሉ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ 21በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት በኢየሩሳሌምም ስለ ቀረችው ዕቃ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 22ወደ ባቢሎን ትወሰዳለች እስከምጐበኛትም ቀን ድረስ በዚያ ትኖራለች፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያን ጊዜም አወጣታለሁ ወደዚህም ስፍራ እመልሳታለሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ