ትንቢተ ኤርምያስ 26
26
1በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ መጣ። 2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ቁም፥ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ ይሰግዱ ዘንድ ለሚመጡት ለይሁዳ ከተሞች ሁሉ ትነግራቸው ዘንድ ያዘዝሁህን ቃል ሁሉ ተናገራቸው፥ አንዲትም ቃል አትጕድል። 3ምናልባት ይሰሙ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፥ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ያሰብሁባቸውን ክፉ ነገር እተዋለሁ። 4እንዲህም በላቸው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በፊታችሁ በሰጠኋት ሕጌ ትሄዱ ዘንድ ባትሰሙኝ፥ 5ያልሰማችሁትን በማለዳ ተነሥቼ ወደ እናንተ የላክኋቸውን የባሪያዎቼን የነቢያትን ቃል ባትሰሙ፥ 6ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርገዋለሁ፥ ይህችንም ከተማ ለምድር አሕዛብ ሁሉ እርግማን አደርጋታለሁ።
7ካህናቱም ነቢያቱም ሕዝቡም ሁሉ ኤርምያስ በእግዚአብሔር ቤት ይህን ቃል ሲናገር ሰሙ። 8ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ነገር ሁሉ በፈጸመ ጊዜ ካህናትና ነቢያት ሕዝቡም ሁሉ፦ ሞትን ትሞታለህ። 9በእግዚአብሔር ስም፦ ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፥ ይህችም ከተማ ባድማና ወና ትሆናለች ብለህ ስለ ምን ትንቢት ተናገርህ? ብለው ያዙት። ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በኤርምያስ ላይ ተሰብስበው ነበር።
10የይሁዳም አለቆች ይህን በሰሙ ጊዜ ከንጉሥ ቤት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፥ በአዲሱም በእግዚአብሔር ቤት ደጅ መግቢያ ተቀመጡ። 11ካህናቱና ነቢያቱም ለአለቆቹና ለሕዝቡ ሁሉ፦ በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁ በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ተናግአልና ይህ ሰው ሞት የሚገባው ነው ብለው ተናገሩ። 12ኤርምያስም ለአለቆችና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ በሰማችሁት ቃል ሁሉ በዚህች ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እናገር ዘንድ እግዚአብሔር ልኮኛል። 13አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል። 14እኔ ግን፥ እነሆ፥ በእጃችሁ ነኝ፥ በዓይናችሁ መልካምና ቅን የመሰለውን አድርጉብኝ። 15ነገር ግን ይህን ቃል ሁሉ በጆሮአችሁ እናገር ዘንድ በእውነት እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛልና ብትገድሉኝ ንጹሕ ደምን በራሳችሁና በዚህች ከተማ በሚኖሩባትም ላይ እንድታመጡ በእርግጥ እወቁ።
16አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፦ ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮናልና ሞት አይገባውም አሉ። 17ከአገሩ ሽማግሌዎችም ሰዎች ተነሥተው ለሕዝቡ ጉባኤ ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ። 18ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ነቢይ ነበረ፥ ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል ብሎ ተናገረ። 19በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ እግዚአብሔርን አልፈሩምን? ወደ እግዚአብሔርስ አልተማለሉምን? እግዚአብሔርስ የተናገረባቸውን ክፉ ነገር አይተውምን? እኛም በነፍሳችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለን።
20ደግሞም በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገረ አንድ ሰው ነበረ፥ እርሱም የቂርያትይዓሪም ሰው የሸማያ ልጅ ኦርዮ ይባል ነበር፥ በዚህችም ከተማ በዚህችም ምድር ላይ እንደ ኤርምያስ ቃል ሁሉ ትንቢት ተናገረ። 21ንጉሡም ኢዮአቄም ኃያላኑም ሁሉ አለቆቹም ሁሉ ቃሉን በሰሙ ጊዜ ንጉሡ ሊገድለው ፈለገ፥ ኦርዮም ይህን በሰማ ጊዜ ፈርቶ ሸሸ ወደ ግብጽም ገባ። 22ንጉሡም ኢዮአቄም የዓክቦርን ልጅ ኤልናታንን ከእርሱም ጋር ሌሎችን ሰዎች ወደ ግብጽ ላካቸው፥ 23ከግብጽም ኦርዮን አውጥተው ወደ ንጉሡ ወደ ኢዮአቄም ይዘውት መጡ፥ እርሱም በሰይፍ ገደለው ሬሳውንም ክቡራን ባልሆኑ ሰዎች መቃብር ጣለው። 24ነገር ግን በሕዝቡ እጅ እንዳይሰጥና እንዳይገድሉት የሳፋን ልጅ የአኪቃም እጅ ከኤርምያስ ጋር ነበረች።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 26: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ