ትንቢተ ኤርምያስ 25
25
1በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በመጀመሪያው ዓመት፥ ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2ይህንም ቃል ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉና በኢየሩሳሌም ለተቀመጡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 3ከይሁዳ ንጉሥ ከአሞጽ ልጅ ከኢዮስያስ ከአሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባሉት በእነዚህ በሀያ ሦስቱ ዓመታት፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፥ እኔም ማልጄ ተነሥቼ ተናገርኋችሁ፥ ነገር ግን አልሰማችሁም። 4እግዚአብሔርም ማልዶ ተነሥቶ ባሪያዎቹን ነቢያትን ወደ እናንተ ላከ፥ እናንተም አላደመጣችሁም ጆሮአችሁንም አላዘነበላችሁም። 5እርሱም፦ ሁላችሁ እናንተ ከክፉ መንገዳችሁና ከሥራችሁ ክፋት ተመለሱ፥ እግዚአብሔርም ከዘላለም ወደ ዘላለም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣችሁ ምድር ተቀመጡ። 6ታመልኩአቸውም ትሰግዱላቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ክፉም እንዳላደርግባችሁ በእጃችሁ ሥራ አታስቈጡኝ አለ። 7ለእናንተ ጕዳት እንዲሆን በእጃችሁ ሥራ ታስቈጡኝ ዘንድ አልሰማችሁኝም፥ ይላል እግዚአብሔር። 8ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቃሌን አልሰማችሁምና እነሆ፥ 9ልኬ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ ባሪያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፥ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፥ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፥ ለመደነቂያና ለማፍዋጫም ለዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ። 10ከእነርሱም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ፥ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። 11ይህችም ምድር ሁሉ ባድማና መደነቂያ ትሆናለች፥ እነዚህም አሕዛብ ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ።
12ሰባው ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ያንን ሕዝብ ስለ ኃጢአታቸው እቀጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የከለዳውያንንም ምድር ለዘላለም ባድማ አደርጋታለሁ። 13በእርስዋም ላይ የተናገርሁትን ቃሌን ሁሉ፥ ማለት ኤርምያስ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ትንቢት የተናገረውን በዚህች መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ፥ በዚያች ምድር አመጣለሁ። 14ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እነርሱን ያስገዙአቸዋል፥ እኔም እንደ አደራረጋቸውና እንደ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ።
15የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፦ የዚህን ቍጣ የወይን ጠጅ ጽዋ ከእጄ ውሰድ አንተንም የምሰድድባቸውን አሕዛብን ሁሉ አጠጣቸው። 16ከምሰድድባቸውም ሰይፍ የተነሣ ይጠጣሉ ይወላገዱማል ያብዳሉም። 17ከእግዚአብሔርም እጅ ጽዋውን ወሰድሁ፥ እግዚአብሔርም እኔን የሰደደባቸውን አሕዛብ ሁሉ አጠጣኋቸው። 18ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ባድማና መደነቂያ ማፍዋጫም እርግማንም አደርጋቸው ዘንድ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ነገሥታትዋንም አለቆችዋንም አጠጣኋቸው። 19የግብጽንም ንጉሥ ፈርዖንን ባሪያዎቹንም አለቆቹንም ሕዝቡንም ሁሉ፥ 20የተደባለቀውንም ሕዝብ ሁሉ፥ የዖፅ ምድር ነገሥታትንም ሁሉ፥ የፍልስጥኤም ምድር ነገሥታትንም ሁሉ አስቀሎናንም ጋዛንም አቃሮንንም የአዛጦንንም ቅሬታ፥ 21ኤዶምያስንም፥ ሞዓብንም፥ የአሞንም ልጆች፥ 22የጤሮስን ነገሥታትም ሁሉ፥ የሲዶናን ነገሥታትም ሁሉ፥ በባህር ማዶ ያለች የደሴት ነገሥታትንም፥ 23ድዳንንም፥ ቴማንንም፥ ቡዝንም፥ ጠጕራቸውንም የሚቈርጡትን ሁሉ፥ 24የዓረብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድረ በዳ የሚቀመጡ የድብልቅ ሕዝብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ 25የዘምሪ ነገሥታትንም ሁሉ፥ የኤላም ነገሥታትንም ሁሉ፥ 26የሜዶን ነገሥታትንም ሁሉ፥ የቀረቡና የራቁ፥ አንዱ ከሌላው ጋር ያሉ የሰሜን ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድር ፊት ላይ ያሉ የዓለም መንግሥታትንም ሁሉ አጠጣኋቸው፥ የሼሻክም ንጉሥ ከእነርሱ በኋላ ይጠጣል።
27አንተም፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመካከላችሁ ከምሰድደው ሰይፍ የተነሣ ጠጡ፥ ስከሩም፥ አስታውኩም ውደቁም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሡም በላቸው። 28ይጠጡም ዘንድ ጽዋውን ከእጅህ ለመቀበል እንቢ ቢሉ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፈጽማችሁ ትጠጣላችሁ በላቸው። 29እነሆ፥ ስሜ የተጠራባትን ከተማ አስጨንቃት ዘንድ እጀምራለሁ፥ በውኑ እናንተ ያልተቀጣችሁ ትሆናላችሁን? በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ያለ ቅጣት አትቀሩም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
30ስለዚህ ይህን ቃል ሁሉ ትንቢት ትናገርባቸዋለህ፥ እንዲህም ትላቸዋለህ፦ እግዚአብሔር በላይ ሆኖ ይጮኻል፥ በቅዱስ ማደሪያውም ሆኖ ድምፁን ያሰማል፥ በበረቱ ላይ እጅግ ይጮኻል፥ ወይንም እንደሚጠምቁ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይጮኻል። 31እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጋር ክርክር አለውና ድምፅ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይደርሳል፥ ከሥጋ ለባሽ ሁሉ ጋር ይፋረዳል፥ ኃጢአተኞችንም ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።
32የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ክፉ ነገር ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ይወጣል፥ ጽኑም ዐውሎ ነፍስ ከምድር ዳርቻ ይነሣል። 33በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ግዳዮች ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ፥ አይለቀስላቸውም፥ በምድር ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ እንጂ አይከማቹም አይቀበሩምም። 34ትታረዱና ትበተኑ ዘንድ ቀናችሁ ደርሶአልና፥ እንደ ተወደደም የሸክላ ዕቃ ትወድቃላችሁና እናንተ እረኞች፥ አልቅሱ ጩኹም፥ እናንተ የመንጋ አውራዎች፥ በአመድ ውስጥ ተንከባለሉ። 35ሽሽትም ከእረኞች ማምለጥም ከመንጋ አውራዎች ይጠፋል። 36እግዚአብሔር ማሰማርያቸውን አጥፍቶአልና የእረኞች ጩኸት ድምፅ የመንጋ አውራዎችም ልቅሶ ሆኖአል። 37ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የተነሣ የሰላም በረት ፈርሶአል። 38እንደ አንበሳ መደቡን ለቅቆአል፥ ከአስጨናቂውም ሰይፍና ከጽኑ ቍጣው የተነሣ ምድራቸው ባድማ ሆናለችና።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 25: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ