የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ፥ እግዚአብሔርም በምድያም እጅ ሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው። የምድያምም እጅ በእስራኤል ላይ ጠነከረች፥ ከምድያምም የተነሣ የእስራኤል ልጆች በተራራ ላይ ጉድጓድና ዋሻ ምሽግም አበጁ። እስራኤልም ዘር በዘሩ ጊዜ ምድያማውያን አማሌቃውያንም በምሥራቅም የሚኖሩ ሰዎች ይመጡባቸው ነበር፥ በእነርሱም ላይ ይሰፍሩ ነበር፥ እስከ ጋዛም ድረስ የምድሩን ቡቃያ ያጠፉ ነበር፥ ምግብንም ለእስራኤል አይተዉም ነበር፥ በግ ወይም በሬ ወይም አህያ ቢሆን አይተዉም። እንስሶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው በብዛት እንደ አንበጣ ሆነው ይመጡ ነበር፥ ለእነርሱና ለግመሎቻቸውም ቁጥር አልነበራቸውም፥ ምድሪቱንም ያጠፉ ዘንድ ይመጡ ነበር። ከምድያምም የተነሣ እስራኤል እጅግ ተጠቁ፥ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እንዲህም ሆነ፥ የእስራኤል ልጆች በምድያም ምክንያት ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ልጆች ነቢይ ላከ፥ እርሱም አለ፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፥ ከባርነትም ቤት አስለቀቅኋችሁ፥ ከግብፃውያንም እጅ፥ ከሚጋፉአችሁም ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ፥ ከፊታችሁም አሳደድኋቸው፥ አገራቸውንም ሰጠኋችሁ፥ እናንተም፦ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፥ በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራያውያንን አማልክት አትፍሩ አልኋችሁ። እናንተ ግን ድምፄን አልሰማችሁም። የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው በአድባሩ ዛፍ በታች ተቀመጠ፥ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጠመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር። የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ፦ አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው። ጌዴዎንም፦ ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው። እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፦ በዚህ በጉልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፥ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው። እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፥ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው። እግዚአብሔርም፦ በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው።
መጽሐፈ መሳፍንት 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 6:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች