እንደ ገና እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ እግዚአብሔርም ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰባት ዓመት ገዟቸው። እስራኤላውያን የምድያማውያን ኀይል ስለ በረታባቸው በየዋሻውና በየምሽጉ፣ በየተራራው ጥግ መሸሸጊያ ስፍራ አበጁ። እስራኤላውያን ዘር በሚዘሩበት ጊዜ ሁሉ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች መጥተው አገሩን ይወሩ ነበር። እነርሱም በምድሪቱ ላይ ሰፍረው እስከ ጋዛ ያለውን ሰብል በማጥፋት አንዳችም የእህል ዘር ለእስራኤል አያስተርፉም፣ የበግም ሆነ የከብት ወይም የአህያ መንጋ አይተዉም ነበር። ከብቶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው ሲመጡ ልክ የአንበጣ መንጋ ይመስሉ ነበር፤ ሰዎቹንም ሆነ ግመሎቻቸውን ለመቍጠር አዳጋች ሲሆን፣ የሚመጡትም ምድሪቱን ለማጥፋት ነበር። ምድያማውያን እስራኤላውያንን ችግር ላይ ስለ ጣሏቸው፣ ይረዳቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። ከምድያማውያን ጥቃት የተነሣ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔር አንድ ነቢይ ላከላቸው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከባርነት ቤት ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ነኝ። ከግብጻውያን እጅ ታደግኋችሁ፤ ከሚያስጨንቋችሁ ሁሉ አዳንኋችሁ፤ እነርሱንም ከፊታችሁ አሳድጄ አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ። እናንተንም፣ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው የአሞራውያንን አማልክት አታምልኩ’ አልኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁኝም።” የእግዚአብሔር መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፣ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፣ ምድያማውያን እንዳያዩበት ደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ፣ “አንተ ኀያል ጦረኛ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነው” አለው። ጌዴዎን መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፣ “ሂድ፤ ባለህ ኀይል እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን?” አለው። ጌዴዎንም፣ “ጌታ ሆይ፤ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተ ሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም፣ “በርግጥ እኔ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው።
መሳፍንት 6 ያንብቡ
ያዳምጡ መሳፍንት 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መሳፍንት 6:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች