መጽሐፈ መሳፍንት 1:27-36

መጽሐፈ መሳፍንት 1:27-36 አማ54

ምናሴም የቤትሳንንና የመንደሮችዋን፥ የታዕናክንና የመንደሮችዋን፥ የዶርንና የመንደሮችዋን፥ የይብለዓምንና የመንደሮችዋን፥ የመጊዶንና የመንደሮችዋን ሰዎች አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ። እስራኤልም በበረቱ ጊዜ ከነዓናውያንን አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላወጡአቸውም። ኤፍሬምም በጌዝር የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው በጌዝር ተቀመጡ። ዛብሎንም የቂድሮንንና የነህሎልን ሰዎች አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው ተቀመጡ፥ ግብርም የሚገብሩለት ሆኑ። አሴርም የዓኮንና የሲዶንን የአሕላብንም የአክዚብንም የሒልባንም የአፌቅንም የረአብንም ሰዎች አላወጣቸውም። በዚያችም ምድር የተቀመጡትን ከነዓናውያን አላወጡአቸውምና በመካከላቸው የአሴር ልጆች ተቀመጡ። ንፍታሌምም የቤትሳምስንና የቤትዓናትን ሰዎች አላወጣቸውም፥ በምድሩም በተቀመጡት በከነዓናውያን መካከል ተቀመጡ፥ ነገር ግን የቤትሳሚስና የቤትዓናት ሰዎች ግብር የሚገብሩለት ሆኑ። አሞራውያንም የዳንን ልጆች ወደ ተራራማው አገር እንዲያፈገፍጉ አስገደዱአቸው፥ ወደ ሸለቆውም እንዳይወርዱ ከለከሉአቸው። አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በኤሎን በሸዓልቢምም በመቀመጥ ጸኑ፥ ነገር ግን የዮሴፍ ቤት እጅ ከበደች፥ አስገበረቻቸውም። የአሞራውያንም ድንበር ከአቅረቢም ዐቀበት ከጭንጫው ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ነበረ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}