ትንቢተ ኢሳይያስ 63
63
1ይህ ከኤዶምያስ፥ ልብሱም የቀላ ከባሶራ የሚመጣ፥ አለባበሱ ያማረ፥ በጕልበቱ ጽናት የሚራመድ ማን ነው? በጽድቅ የምናገር ለማዳንም የምበረታ እኔ ነኝ። 2ቀሚስህ ስለ ምን ቀላ? ልብስህስ በወይን መጥመቂያ እንደሚረግጥ ሰው ልብስ ስለ ምን መሰለ? 3መጥመቂያውን ብቻዬን ረግጫለሁ፥ ከአሕዛብም አንድ ሰው ከእኔ ጋር አልነበረም፥ በቍጣዬ ረገጥኋቸው በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፥ ደማቸዋም በልብሴ ላይ ተረጭቶአል፥ ልብሴንም ሁሉ አሳድፌአለሁ። 4የምበቀልበት ቀን በልቤ ነውና፥ የምቤዥበትም ዓመት ደርሶአልና። 5ተመለከትሁ፥ የሚረዳም አልተገኘም፥ የሚያግዝም አልነበረምና ተደነቅሁ፥ ስለዚህ የገዛ ክንዴ መድኃኒት አመጣልኝ፥ ቍጣዬም እርሱ አገዘኝ። 6በቍጣዬም አሕዛብን ረገጥሁ በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፥ ደማቸውንም ወደ ምድር አፈሰስሁት። 7እግዚአብሔር እንደ ሰጠን ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የእግዚአብሔርን ምስጋና፥ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን ትልቅ በጎነት አሳስባለሁ። 8እርሱም፦ በእውነት ሕዝቤ፥ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች፥ ናቸው አለ፥ መድኃኒትም ሆነላቸው። 9በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፥ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው። 10እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፥ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፥ እርሱም ተዋጋቸው። 11እርሱም እንዲህ ብሎ የቀደመውን ዘመን አሰበ፦ የበጎቹን እረኛ ከባሕሩ ያወጣው ወዴት ነው ያለ? ቅዱስ መንፈሱንም በመካከላቸው ያኖረ ወዴት ነው ያለ? 12የከበረውንም ክንድ በሙሴ ቀኝ ያስሄደ፥ ለራሱም የዘላለምን ስም ያደርግ ዘንድ ውኃውን በፊታቸው የከፈለ፥ 13በምድረ በዳም እንደሚያልፍ ፈረስ፥ በቀላይ ውስጥ ያለ እንቅፋት ያሳለፋቸው ወዴት ነው ያለ? 14ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፥ እንዲሁ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው፥ እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስም ታደርግ ዘንድ ሕዝብን መራህ። 15ከሰማይ ተመልከት፥ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ፥ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ተከለከለ። 16አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፥ አቤቱ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው። 17አቤቱ፥ ከመንገድህ ለምን አሳትኸን? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ ባሪያዎችህ ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ። 18የተቀደሰው ሕዝብህ መቅደስህን ጥቂት ጊዜ ወረሱት፥ ጠላቶቻችንም ረግጠውታል። 19ከዘላለም እንዳልገዛኸን በስምህም እንዳልተጠራን ሆነናል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 63: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ