የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 62

62
1ስለ ጽዮን ዝም አልልም፥ ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም፥ ጽድቅዋ እንደ ጸዳል መዳንዋም እንደሚበራ ፋና እስኪወጣ ድረስ። 2አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፥ የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ። 3በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፥ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ። 4ከእንግዲህ ወዲህ፦ የተተወች አትባዪም፥ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ፦ ውድማ አትባልም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ብሎታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ፦ ደስታዬ የሚኖርባት ትባያለሽ ምድርሽም፦ ባል ያገባች ትባላለች። 5ጕልማሳም ድንግሊቱን እንደሚያገባ፥ እንዲሁ ልጆችሽ ያገቡሻል፥ ሙሽራም በሙሽራይቱ ደስ እንደሚለው፥ እንዲሁ አምላክሽ በአንቺ ደስ ይለዋል። 6-7ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ጕበኞችን በቅጥርሽ ላይ አቁሜአለሁ፥ ቀንና ሌሊት ከቶ ዝም አይሉም፥ እናንተ እግዚአብሔርን የምታሳስቡ፥ ኢየሩሳሌምን እስኪያጸና በምድርም ላይ ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ አትረፉ ለእርሱም ዕረፍት አትስጡ። 8እግዚአብሔር፦ ከእንግዲህ ወዲህ በእርግጥ ለጠላቶችሽ መብል ይሆን ዘንድ እህልሽን አልሰጥም፥ መጻተኞችም የደከምሽበትን ወይንሽን አይጠጡም፥ 9ነገር ግን የሰበሰቡት ይበሉታል እግዚአብሔርንም ያመሰግናሉ፥ ያከማቹትም በመቅደሴ አደባባይ ላይ ይጠጡታል ብሎ በቀኙና በኃይሉ ክንድ ምሎአል። 10እለፉ፥ በበሮች በኩል እለፉ፥ የሕዝቡንም መንገድ ጥረጉ፥ አዘጋጁ፥ ጎዳናውን አዘጋጁ፥ ድንጋዮቹንም አስወግዱ፥ ለአሕዛብም ዓላማ አነሡ። 11እነሆ፥ እግዚአብሔር ለምድር ዳርቻ አዋጅ እንዲህ ብሎ ነግሮአል፦ ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ መድኃኒትሽ ይመጣል፥ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ አለ በሉአት። 12እግዚአብሔር፦ የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ ብለው ይጠሩአቸዋል፥ አንቺም፦ የተፈለገች ያልተተወችም ከተማ ትባያለሽ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ