ትንቢተ ኢሳይያስ 64
64
1ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ! 2እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፥ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፥ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ ዘንድ፥ አህዛብም በፊትህ ይንቀጠቀጡ ዘንድ። 3ያልተጠባበቅነውን የክብርህን ሥራ ባደረግህ ጊዜ፥ ወረድህ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ። 4ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላችው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም። 5ጽድቅን የሚያደርገውን በመንገዶችህም የሚያስቡህን ትገናኛቸዋለህ። እነሆ፥ አንተ ተቈጣህ እኛም ኃጢአት ሠራን፥ ስለዚህም ተሳሳትን። 6ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፥ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። 7ስምህንም የሚጠራ፥ አንተንም ሊይዝ የሚያስብ የለም፥ ፊትህንም ከእኛ ሰውረሃል፥ በኃጢአታችንም አጥፍተኸናል። 8አሁን ግን፥ አቤቱ፥ እንተ አባታችን ነህ፥ እኛ ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ፥ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን። 9አቤቱ፥ እጅግ አትቈጣ፥ ለዘላለምም ኃጢአትን አታስብ፥ እነሆ፥ እባክህ፥ ተመልከት፥ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነን። 10የተቀደሱ ከተሞችህ ምድረ በዳ ሆነዋል፥ ጽዮን ምድረ በዳ ኢየሩሳሌምም ውድማ ሆናለች። 11አባቶቻችን አንተን ያመሰገኑበት የተቀደሰና የተዋበ ቤታችን በእሳት ተቃጥሎአል፥ ያማረውም ስፍራችን ሁሉ ፈርሶአል። 12አቤቱ፥ በውኑ በዚህ ነገር ትታገሣለህን? ዝምስ ትላለህን? አጥብቀህስ ታስጨንቀናለህን?
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 64: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ