የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 56

56
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ማዳኔ ሊመጣ ጽድቄም ሊገለጥ ቀርቦአልና ፍርድን ጠብቁ ጽድቅንም አድረጉ። 2ይህን የሚያደርግ ሰው ይህንንም የሚይዝ የሰው ልጅ፥ እንዳያረክሰው ሰንበትንም የሚጠብቅ እጁንም ክፋት ከማድረግ የሚጠብቅ ብፁዕ ነው። 3ወደ እግዚአብሔርም የተጠጋ መጻተኛ፦ በእውነት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ይለየኛል አይበል፥ ጃንደረባም፦ እነሆ፥ እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ አይበል። 4እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና፦ 5በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፥ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ። 6ያገለግሉት ዘንድ የእግዚአብሔርንም ስም ይወድዱ ዘንድ ባሪያዎቹም ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚጠጉትንም መጻተኞች፥ እንዳያረክሱት ሰንበትን የሚጠብቁትን ቃል ኪዳኔንም የሚይዙትን ሁሉ፥ 7ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፥ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፥ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና ሌላ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያዬ ላይ እቀበላለሁ። 8ከእስራኤል የተበተኑትን የሚሰበስብ ጌታ እግዚአብሔር፦ ወደ ተሰበሰቡት ዘንድ ሌሎችን እሰበስብለታለሁ ይላል። 9እናንተ የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ፥ እናንተም የዱር አራዊት ሁሉ፥ ትበሉ ዘንድ ቅረቡ። 10ጕበኞቹ ዕውሮች ናቸው፥ ሁሉ ያለ እውቀት ናቸው፥ ሁሉም ዲዳ የሆኑ ውሾች ናቸው ይጮኹም ዘንድ አይችሉም፥ ሕልምን ያልማሉ፥ ይተኛሉ፥ ማንቀላፋትም ይወድዳሉ። 11መብል ወዳጆች ከቶ የማይጠግቡ ውሾች ናቸው፥ እነርሱም ያስተውሉ ዘንድ የማይችሉ እረኞች ናቸው፥ ሁሉ ወደ መንገዳቸው፥ ከፊተኛው እስከ ኋለኛው ድረስ ሁሉ፥ እያንዳንዳቸው ወደ ጥቅማቸው ዘወር ብለዋል። 12ኑ የወይን ጠጅ እንውሰድ፥ በሚያሰክርም መጠጥ እንርካ፥ ዛሬም እንደ ሆነ እንዲሁ ነገ ይሆናል፥ ከዛሬም ይልቅ እጅግ ይበልጣል ይላሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ