ትንቢተ ኢሳይያስ 55
55
1እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፥ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። 2ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። 3ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፥ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች፥ የታመነችይቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘላለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። 4እነሆ፥ ለአሕዛብ ምስክር፥ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ። 5እነሆ፥ የማታውቀውን ሕዝብ ትጠራለህ፥ የእስራኤልም ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ እግዚአብሔር የማያውቁህ ሕዝብ ወደ አንተ ይሮጣሉ። 6እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፥ 7ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፥ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ። 8አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር። 9ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። 10ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ 11ከአፌ የሚወጣ ቃል እንዲሁ ይሆናል፥ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም። 12እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፥ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልልታ ያደርጋሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። 13በእሾህም ፈንታ ጥድ በኵርንችትም ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል፥ ለእግዚአብሔርም መታሰቢያና ለዘላለምም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 55: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ