የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 45:1-7

ትንቢተ ኢሳይያስ 45:1-7 አማ54

እግዚአብሔር ለቀባሁት፥ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ወገብ እፈታ ዘንድ፥ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፥ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል፦ በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም አደርጋለሁ፥ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፥ በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ። ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፥ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፥ በቍልምጫ ስምህ ጠራሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፥ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፥ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም። ብርሃንን ሠራሁ፥ ጨለማውንም ፈጠርሁ፥ ደኅንነትን እሠራለሁ፥ ክፋትንም እፈጥራለሁ፥ እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።