የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 45

45
1እግዚአብሔር ለቀባሁት፥ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ወገብ እፈታ ዘንድ፥ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፥ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል፦ 2በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም አደርጋለሁ፥ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፥ 3በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ። 4ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፥ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፥ በቍልምጫ ስምህ ጠራሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም። 5-6እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፥ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፥ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም። 7ብርሃንን ሠራሁ፥ ጨለማውንም ፈጠርሁ፥ ደኅንነትን እሠራለሁ፥ ክፋትንም እፈጥራለሁ፥ እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። 8እናንተ ሰማያት ከላይ አንጠባጥቡ ደመናትም ጽድቅን ያዝንቡ፥ ምድርም ትከፈት መድኃኒትንም ታብቅል፥ ጽድቅም በአንድነት ይብቀል፥ እኔ እግዚአብሔር ፈጥሬዋለሁ። 9ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት! በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው። ጭቃ ሠሪውን፦ ምን ትሠራለህ? ወይስ ሥራህ፦ እጅ የለውም ይላልን? 10አባትን፦ ምን ወልደሃል? ወይም ሴትን፦ ምን አማጥሽ? ለሚል ወዮ! 11የእስራኤል ቅዱስ ሠሪውም እንዲህ ይላል፦ ስለሚመጣው ነገር ጠይቁኝ፥ ስለ ልጆቼና ስለ እጄ ሥራም እዘዙኝ። 12እኔ ምድርን ሠርቻለሁ ሰውንም በእርስዋ ላይ ፈጥሬአለሁ፥ እኔ በእጄ ሰማያትን ዘርግቻለሁ፥ ሠራዊታቸውንም ሁሉ አዝዣለሁ። 13እኔ በጽድቅ አስነሥቼዋለሁ መንገዱንም ሁሉ አቀናለሁ፥ እርሱ ከተማዬን ይሠራል፥ በዋጋም ወይም በደመወዝ ሳይሆን ምርኮኞቼን ያወጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 14እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የግብፅ ድካምና የኢትዮጵያ ንግድ ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፥ ለአንተም ይሆናሉ እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል፥ በፊትህም ያልፋሉ፥ ለአንተም እየሰገዱ፦ በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል። 15የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ፥ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ። 16ሁሉም ያፍራሉ ይዋረዱማል፥ ጣዖታትንም የሚሠሩ በአንድነት ወደ ውርደት ይሄዳሉ። 17እግዚአብሔር ግን እስራኤልን በዘላለማዊ መድኃኒት ያድነዋል፥ እናንተም ለዘላለም አታፍሩምና አትዋረዱም። 18ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል፦ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም። 19በስውር ወይም በጨለማ ምድር ሥፍራ አልተናገርሁም፥ ለያዕቆብ ዘር፦ በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም፥ እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ ቅንንም አወራለሁ። 20እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፥ ተሰብስባችሁ ኑ በአንድነትም ቅረቡ፥ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ እውቀት የላቸውም። 21ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ፥ ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፥ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፥ ከእኔም በቀር ማንም የለም። 22እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። 23ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም፦ ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ። 24ስለ እኔም፦ በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ጽድቅና ኃይል አለ፥ ወደ እርሱም ሰዎች ይመጣሉ፥ በእርሱም ላይ የተቆጡ ሁሉ ያፍራሉ። 25የእስራኤልም ዘር ሁሉ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፥ ይመካሉም ይባላል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ