ትንቢተ ኢሳይያስ 46
46
1ቤል ተዋረደ፥ ናባው ተሰባበረ፥ ጣዖቶቻቸው በእንስሳና በከብት ላይ ተጭነዋል፥ ሸክሞቻችሁ ለደካማ እንስሳ ከባድ ጭነት ሆነዋል። 2ተጐነበሱ በአንድነትም ተዋረዱ፥ ሸክሙን ለማዳን አልቻሉም፥ ራሳቸው ግን ተማረኩ። 3እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ የእስራኤልም ቤት ቅሬታ ሁሉ፥ ከሆድ ያነሣኋችሁ ከማኅፀንም የተሸከምኋችሁ፥ ስሙኝ። 4እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፥ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፥ እኔ ሠርቻለሁ እኔም አነሣለሁ፥ እኔ እሸከማለሁ እኔም አድናለሁ። 5በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ? 6ወርቁን ከኮሮጆ የሚያፈስሱ ብሩንም በሚዛን የሚመዝኑ እነርሱ አንጥረኛውን ይቀጥራሉ፥ እርሱም አምላክ አድርጎ ይሠራዋል፥ ለዚያም ይጐነበሱለታል ይሰጉለትማል። 7በጫንቃቸው ላይ አንሥተው ይሸከሙታል በስፍራውም ያደርጉታል፥ በዚያም ይቆማል፥ ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም፥ ሰውም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይሰማውም ከመከራውም አያድነውም። 8ይህን አስቡና አልቅሱ፥ ተላላፊዎች ሆይ፥ ንስሐ ግቡ፥ ልባችሁንም መልሱ። 9እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። 10በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፥ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ። 11ከምሥራቅ ነጣቂ ወፍን፥ ከሩቅም አገር ምክሬን የሚያደርገውን ሰው እጠራለሁ። ተናግሬአለሁ እፈጽምማለሁ፥ አስቤአለሁ አደርግማለሁ። 12እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ እልከኞች፥ ስሙኝ፥ 13ጽድቄን አቀርባለሁ፥ አይርቅም መድኃኒቴም አይዘገይም፥ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቼአለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 46: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ