የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 47

47
1አንቺ ድንግል የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ውረጂ በትቢያም ላይ ተቀመጪ፥ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ ከዚህ በኋላ ቅልጣናምና ቅምጥል አትባይምና ያለ ዙፋን በመሬት ላይ ተቀመጪ። 2ወፍጮ ወስደሽ ዱቄትን ፍጪ፥ መሸፈኛሽን አውጪ ረጅሙንም ልብስሽን አውልቀሽ ጣይው፥ ባትሽን ግለጪ፥ ወንዙን ተሻገሪ። 3ኀፍረተ ሥጋሽ ይገለጣል እፍረትሽም ይታያል፥ እኔ እበቀላለሁ፥ ለማንም አልራራም። 4ታዳጊያችን፥ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ ነው። 5የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፥ ከዚህ በኋላ፦ የመንግሥታት እመቤት አትባይምና ዝም ብለሽ ተቀመጪ ወደ ጨለማም ውስጥ ግቢ። 6በሕዝቤ ላይ ተቈጥቼ ነበር ርስቴንም አረከስሁ በእጅሽም አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ ከእነርሱ ጋር ምሕረት አላደረግሽም፥ በሽማግሌዎቻቸው ላይ ቀንበርሽን እጅግ አክብደሻል። 7አንቺም፦ እኔ ለዘላለም እመቤት እሆናለሁ ብለሻል፥ ይህንም በልብሽ አላደረግሽም ፍጻሜውንም አላሰብሽም። 8አሁንም አንቺ ቅምጥል ተዘልለሽ የምትቀመጪ፥ በልብሽም፦ እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፥ መበለትም ሆኜ አልኖርም የወላድ መካንነትንም አላውቅም የምትዪ ይህን ስሚ፥ 9አሁን ግን በአንድ ቀን እነዚህ ሁለት ነገሮች፥ የወላድ መካንነትና መበለትነት፥ በድንገት ይመጡብሻል፥ ስለ መተቶችሽ ብዛትና ስለ አስማቶችሽ ጽናት ፈጽመው ይመጡብሻል። 10በክፋትሽ ታምነሻል፥ የሚያየኝ የለም ብለሻል፥ ጥበብሽና እውቀትሽ አታልለውሻል፥ በልብሽም፦ እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም ብለሻል። 11ስለዚህ ምክንያት ክፉ ነገር ይመጣብሻል፥ በምዋርትሽም እንዴት እንደምታርቂው አታውቂም፥ ጉዳት ይወድቅብሻል ታስወግጂውም ዘንድ አይቻልሽም፥ የማታውቂያትም ጕስቍልና ድንገት ትመጣብሻለች። 12ምናልባትም መጠቀም ትችዪ ወይም ታስደነግጪ እንደ ሆነ፥ ከአስማቶችሽና ከሕፃንነትሽ ጀምረሽ ከደከምሽበት ከመተቶችሽ ብዛት ጋር ቁሚ። 13በምክርሽ ብዛት ደክመሻል፥ አሁንም የሰማይን ከዋክብት የሚቈጥሩ፥ ከዋክብትንም የሚመለከቱ፥ በየመባቻውም የሚመጣውን ነገር የሚናገሩ ተነሥተው ከሚመጣብሽ ነገር ያድኑሽ። 14እነሆ፥ እንደ እብቅ ይሆናሉ፥ እሳትም ያቃጥላቸዋል ሰውነታቸውንም ከነበልባል ኃይል አያድኑም፥ እርሱም ሰው እንደሚሞቀው ፊም፥ ወይም በፊቱ ሰው እንደሚቀመጥበት እሳት ያለ አይደለም። 15የደከምሽባቸው ነገሮች እንዲህ ይሆኑብሻል፥ ከሕፃንነትሽ ጀምረው ከእንቺ ጋር ይነግዱ የነበሩ እያንዳንዳቸው ወደ ስፍራቸው ይሄዳሉ፥ የሚያድንሽም የለም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ