አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል አምላካችሁ። ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ፥ የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፥ ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ፥ ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች ወደ እርስዋ ጩኹ። የአዋጅ ነጋሪ ቃል፦ የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጎዳና በበረሀ አስተካክሉ። ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፥ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፥ የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። ጩኽ የሚል ሰው ቃል፥ ምን ብዬ ልጩኽ? አልሁ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው። ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ ያምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች። የምስራች የምትነግሪ ጽዮን ሆይ፥ ከፍ ወደለው ተራራ ውጪ፥ የምስራች የምትነግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ድምፅሽን በኃይል አንሺ፥ አንሺ፥ አትፍሪ፥ ለይሁዳም ከተሞች፦ እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለሽ ንገሪ። እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፥ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው። መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።
ትንቢተ ኢሳይያስ 40 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 40:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos