የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 40:1-11

ትንቢተ ኢሳይያስ 40:1-11 አማ05

እግዚአብሔር አምላካችሁ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤን አጽናኑ! ሕዝቤን አጽናኑ! የባርነት ጊዜዋ እንዳለቀ፥ ለፈጸመችው ኃጢአት ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ እጥፍ ቅጣት እንደ ተቀበለችና ኃጢአትዋም ይቅር እንደ ተባለላት ለኢየሩሳሌም በለሰለሰ አነጋገር ንገሯት።” እንዲህ የሚል ድምፅ ይሰማል፦ “በምድረ በዳ የእግዚአብሔርን መንገድ አዘጋጁ! በበረሓም ለአምላካችን ጥርጊያ ጐዳና አብጁ! ጐድጓዳውና ሸለቆው ይሙላ፤ ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ብሎ ይደልደል፤ ኮረብታውና ወጣ ገባ የሆነው ምድር ሁሉ ይስተካከል። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር ክብር ይገለጣል፤ እግዚአብሔር ይህን የተናገረ ስለ ሆነ ሰዎች ሁሉ ይህን በአንድነት ሆነው ያዩታል።” አንድ ድምፅ “የዐዋጅ ቃል ተናገር!” እያለ ይጮኻል። እኔም “ምን ብዬ ላውጅ!” ስል ጠየቅሁ። ያም ድምፅ “እንዲህ ብለህ ዐውጅ” አለኝ፦ “ሰው ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው፤ የእግዚአብሔር ነፋስ በሚነፍስበት ጊዜ፥ ሣሩ እንደሚደርቅና አበባውም እንደሚረግፍ ሰውም እንዲሁ ረጋፊ ነው። በእርግጥ ሣር ይደርቃል፤ አበባም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።” ለጽዮን መልካም ነገርን የምታበሥሩ ሆይ! ወደ ከፍተኛ ተራራ ውጡ! እናንተ ለኢየሩሳሌም መልካም ዜናን የምታበሥሩ ሆይ! ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ! ጮክ በሉ አትፍሩ! ለይሁዳ ከተሞች፥ “እነሆ፥ አምላካችሁ” በሉ። እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር በታላቅ ኀይሉ ለመግዛት ይመጣል፤ የሚመጣውም የሚሰጠውን ሽልማትና የሚከፍለውን የሥራ ዋጋ ይዞ ነው። እንደ እረኛ ለመንጋው እንክብካቤ ያደርጋል፤ ግልገሎቹን በአንድነት ይሰበስባል፤ በእጆቹም ዐቅፎ ይወስዳቸዋል፤ እናቶቻቸውንም በርኅራኄ ይመራቸዋል።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}