ትንቢተ ኢሳይያስ 3:1-15

ትንቢተ ኢሳይያስ 3:1-15 አማ54

እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፍንና ብርታትን፥ የእንጀራን ድጋፍ ሁሉ የውሃውንም ድጋፍ ሁሉ፥ ኃያሉንም፥ ተዋጊውንም፥ ፈራጁንም፥ ነብዩንም፥ ምዋርተኛውንም፥ ሽማግሌውንም፥ የአምሳ አለቃውንም፥ ከበርቴውን፥ አማካሪውንም፥ ብልሁንም ሠራተኛ፥ አስማት አዋቂውንም ይነቅላል። አለቆቻቸው እንዲሆኑ ብላቴኖችን አስነሣባቸዋለሁ፥ ሕፃናቶችም ይገዙአቸዋል። ሕዝቡም፥ ሰው በሰው ላይ ሰውም በባልንጀራው ላይ፥ ይገፋፋል፥ ብላቴናውም በሽማግሌው ላይ የተጠቃውም በከበርቴው ላይ ይኮራል። ሰውም በአባቱ ቤት ውስጥ ወንድሙን ይዞ፦ አንተ ልብስ አለህ አለቃም ሁንልን ይህችም ባድማ ከእጅህ በታች ትሁን ሲለው፥ በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ፦ እኔ በቤቴ ውስጥ እንጀራ ወይም ልብስ የለኝምና ባለ መድኃኒት አልሆንም፥ በሕዝቡም ላይ አለቃ አታደርጉኝም ይላል። የክብሩን ዓይን ያስቈጡ ዘንድ ምላሳቸውና ሥራቸው በእግዚአብሔር ላይ ነውና ኢየሩሳሌም ተፈታች ይሁዳም ወደቀ። የፊታቸውም እፍረት ይመሰክርባቸዋል፥ እንደ ሰዶምም ኃጢአታቸውን ያወራሉ፥ አይሠውሩአትም። በራሳቸው ላይ ክፉ ነገርን ሠርተዋልና ለነፍሳቸው ወዮ! የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና ጻድቁን፦ መልካም ይሆንልሃል በሉት። እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ደርሶበታል። ሕዝቤንስ አስገባሪዎቻቸው ይገፍፉአቸዋል፥ አስጨናቂዎችም ይሠለጥኑባቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፥ የመሩአችሁ ያስቱአችኋል የምትሄዱበትንም መንገድ ያጠፋሉ። እግዚአብሔር ለፍርድ ተነሥቶአል በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ቆሞአል። እግዚአብሔር ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከአለቆቻቸው ጋር ይፋረዳል፥ የወይኑን ቦታ የጨረሳችሁ እናንተ ናችሁ፥ ከድሆች የበዘበዛችሁት በቤታችሁ አለ፥ ሕዝቤንም ለምን ታደቅቁአቸዋላችሁ? የድሆችንስ ፊት ለምን ትፈጫላችሁ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።