ትንቢተ ኢሳይያስ 3:1-15

ትንቢተ ኢሳይያስ 3:1-15 አማ05

እነሆ ጌታ የሠራዊት አምላክ፥ ሕዝቡ ኀይልና ብርታት አግኝተው የሚኖሩበትን ምግብና ውሃ፥ ሌላም ነገር ሁሉ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ያስወግዳል። ጀግኖቻቸውን፥ ወታደሮቻቸውን፥ ዳኞቻቸውንና ነቢያታቸውን፥ ሟርተኞቻቸውንና ሽማግሌዎቻቸውን፥ የጦር መኰንኖቻቸውንና አማካሪዎቻቸውን፥ ጠንቋዮቻቸውንና የወደፊቱን እናውቃለን የሚሉትን ሁሉ ነቃቅሎ ያጠፋል። ገና ታዳጊ የሆኑና በዕድሜ ያልጠኑ ልጆችንም መሪዎች አድርጎ ይሾምባቸዋል። ሕዝቡም እርስ በርሱ አንዱ ሌላውን ለመጨቈን ባልንጀራ በባልንጀራው ላይ ይነሣሣል፤ ወጣቱ ሽማግሌውን አያከብርም፤ ተንቆ ይኖር የነበረውም ሰው ክብር ባለው ሰው ላይ ይታበያል። የቤተሰብ አባላት በአባታቸው ቤት አንዱን ወንድማቸውን መርጠው “አንተ ሌላው ቢቀር እንኳ የምትለብሰው ልብስ አለህ፤ ስለዚህ እባክህ አለቃችን ሁን፤ ፍርስራሽ ሁሉ በአንተ ሥልጣን ሥር ይሁን” ይሉታል። እርሱም በዚያን ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ “እኔም ብሆን በቤቴ ውስጥ የበቃ ምግብም ሆነ ልብስ ስለሌለኝ መፍትሔ ላስገኝላችሁ አልችልም! ስለዚህ መሪ አታድርጉኝ!” ሲል ይመልስላቸዋል። ኢየሩሳሌም ተሰናክላ በመንገዳገድ ላይ ናት፤ ይሁዳም ልትወድቅ ተቃርባለች፤ ምክንያቱም የሚናገሩትም ሆነ የሚሠሩት ሁሉ እግዚአብሔርን በመፈታተን ስለ ሆነ ክብሩን አቃለዋል። ለሚመለከታቸው ሰው ፊታቸው ይመሰክርባቸዋል፤ እንደ ሰዶም ሰዎች ሳይደብቁ ኃጢአታቸውን በግልጽ ይናገራሉ፤ በራሳቸው ላይ ጥፋትን ስላመጡ ወዮላቸው። ሁሉ ነገር ስለሚሳካላቸውና የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ስለሚያገኙ ጻድቃንን የተባረካችሁ ናችሁ በሉአቸው። ምንም ነገር ስለማይሳካላቸውና የክፉ ተግባራቸውን ዋጋ ስለሚያገኙ ለክፉዎች ወዮላቸው! ገንዘብ አበዳሪዎች ሕዝቤን ያራቊታሉ፤ አራጣ አበዳሪዎችም ይበዘብዙአቸዋል፤ ሕዝቤ ሆይ፥ መሪዎቻችሁ ያስቱአችኋል፤ የምትሄዱበትንም መንገድ ያጣምማሉ። እግዚአብሔር በፍርድ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦአል፤ በሕዝቡም ላይ ለመፍረድ ተዘጋጅቶአል። ስለዚህ የሕዝቡን መሪዎችና አማካሪዎች ወደ ፍርድ አቅርቦ እንዲህ ይላቸዋል፦ “የወይኑን አትክልት ቦታ ዘረፋችሁ፤ ከድኾች በተዘረፈው ሀብትም ቤታችሁን ሞላችሁ። የሕዝቤን ቅስም ልትሰብሩና ድኾችንም ልትበዘብዙ መብት የላችሁም፤ ይህን የተናገርኩ እኔ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነኝ።”