የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 29

29
1ዳዊት ለሰፈረባት ከተማ ለአርኤል ወዮላት! ዓመት በዓመት ላይ ጨምሩ፥ በዓላትም ይመለሱ። 2አርኤልንም አስጨንቃለሁ፥ ልቅሶና ዋይታም ይሆንባታል፥ እንደ አርኤልም ትሆንልኛለች። 3በዙሪያሽም እሰፍራለሁ፥ በቅጥርም ከብቤ አስጨንቅሻለሁ፥ አምባም በላይሽ አቆማለሁ። 4ትዋረጅማለሽ፥ በመሬትም ላይ ሆነሽ ትናገሪያለሽ፥ ቃልሽም ዝቅ ብሎ ከአፈር ይወጣል፥ ድምጽሽም ከመሬት እንደሚወጣ እንደ መንፍስት ጠሪ ድምፅ ይሆናል፥ ቃልሽም ከአፈር ወጥቶ ይጮኸል። 5ነገር ግን የጠላቶችሽ ብዛት እንደ ደቀቀ ትቢያ፥ የጨካኞችም ብዛት እንደሚያልፍ ገለባ ይሆናል። 6ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅም ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል። 7በአርኤልም ላይ የሚዋጉ፥ እርስዋንና ምሽግዋንም የሚወጉ የሚያስጨንቋትም፥ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደ ሕልምና እንደ ሌሊት ራእይ ይሆናል። 8ተርቦም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፥ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይበላል፥ ነገር ግን ይነቃል ሰውነቱም ባዶ ነው፥ ተጠምቶም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፥ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይጠጣል፥ ነገር ግን ይነቃል፥ እነሆም፥ ይዝላል ሰውነቱም አምሮት አለው፥ እንዲሁም የጽዮንን ተራራ የሚወጉ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት ይሆናል። 9ተደነቁ ደንግጡም፥ ተጨፈኑም ዕውሮችም ሁኑ፥ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ስከሩ፥ በሚያሰክር መጠጥ እይሁን እንጂ ተንገደገዱ። 10እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል ዓይኖቻችሁን ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል። 11ራእዩም ሁሉ እንደ ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፥ ማንበብንም ለሚያውቅ፦ ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፦ ታትሞአልና አልችልም ይላቸዋል፥ 12ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ፦ ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፦ ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል። 13ጌታም፦ ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈሮቹም ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና 14ስለዚህ፥ እነሆ፥ ድንቅ ነገርን በዚህ ሕዝብ መካከል፥ ድንቅ ነገርን ተአምራትንም፥ እንደ ገና አደርጋለሁ፥ የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለች፥ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች። 15ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር ለሚሰውሩ፥ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው፦ ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል? ለሚሉ ወዮላቸው! 16ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን፦ አልሠራኸኝም ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን፦ አታስተውልም ይለዋልን? 17ሊባኖስ እንደ ፍሬያማ እርሻ ሊለወጥ ፍሬያማውም እርሻ እንደ ዱር ሊቆጠር ጥቂት ዘመን የቀረ አይደለምን? 18በዚያም ቀን ደንቆሮች የመጽሐፍን ቃል ይሰማሉ፥ የዕውሮችም ዓይኖች ከጭጋግና ከጨለማ ተለይተው ያያሉ። 19የዋሃን ደስታቸውን በእግዚአብሔር ያበዛሉ፥ በሰዎች መካከል ያሉ ችግረኞችም ሐሤትን በእስራኤል ቅዱስ ያደርጋሉ። 20ጨካኙ ሰው አልቆአልና፥ ፌዘኛውም ጠፍቷልና፥ ለኃጢአትም የደፈጡ ሁሉ ይቈረጣሉና፥ 21እነዚህም ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፥ በበርም ለሚገሥጸው አሽክላ የሚያኖሩ፥ ጻድቁንም በከንቱ ነገር የሚያስቱ ናቸው። 22ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠ እግዚአብሔር ስለ ያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፦ ያዕቆብ አሁን አያፍርም፥ ፊቱም አሁን አይለወጥም። 23ነገር ግን የእጄን ሥራ ልጆቹን በመካከሉ ባያቸው ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፥ የያዕቆብንም ቅዱስ ይቀድሳሉ፥ 24የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ። በመንፈስም የሳቱ ማስተዋልን ያውቃሉ፥ የሚያጕረመርሙ ትምህርትን ይቀበላሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ