ትንቢተ ኢሳይያስ 30
30
1ለዓመፀኞች ልጆች ወዮላቸው! ይላል እግዚአብሔር፥ ከእኔ ዘንድ ያልሆነን ምክር ይመክራሉ፥ ኃጢአትንም በኃጢአት ላይ ይጨምሩ ዘንድ ከመንፈሴ ዘንድ ያልሆነውን ቃል ኪዳን ያደርጋሉ። 2ከአፌ ነገርን ሳይጠይቁ በፈርዖን ኃይል ይጸኑ ዘንድ በግብጽም ጥላ ይታመኑ ዘንድ ወደ ግብጽ እንዲወርዱ ይሄዳሉ። 3ስለዚህ የፈርዖን ኃይል እፍረት በግብጽም ጥላ መታመን ስድብ ይሆንባችኋል። 4አለቆች ምንም በጣኔዎስ ቢሆኑ፥ መልእክተኞችም ምንም ወደ ሐኔስ ቢደርሱ፥ 5ሁላቸው ይጠቅሟቸው ዘንድ ስለማይችሉ፥ እፍረትና ስድብ እንጂ ረድኤትና ረብ ስለማይሆኑ ሕዝብ ያፍራሉ። 6በደቡብ ስላሉ እንስሶች የተነገረ ሸክም። ተባትና እንስት አንበሳ እፉኝትም ነዘር እባብም በሚወጡባት በመከራና በጭንቀት ምድር በኩል ብልጥግናቸውን በአህዮች ጫንቃ ላይ መዛግብቶቻቸውንም በግመሎች ሻኛ ላይ እየጫኑ ወደማይጠቅሙአቸው ሕዝብ ይሄዳሉ። 7የግብጽ እርዳታ ከንቱና ምና ምን ነው፥ ስለዚህ ስሙን፦ በቤት የሚቀመጥ ረዓብ ብዬ ጠርቼዋለሁ። 8አሁንም ሂድ፥ ለሚመጣውም ዘመን ለዘላለም እንዲሆን በሰሌዳ ላይ በመጽሐፍም ውስጥ ጻፍላቸው። 9ዓመጸኛ ወገንና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመስማት የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና፥ 10ባለ ራእዮችን፦ አትመልከቱ ይላሉ፥ ነቢያትንም፦ ጣፋጩንና አታላዩን ነገር እንጂ ቅኑን ነገር አትንገሩን፥ 11ከመንገድ ፈቀቅ በሉ፥ ከጐዳናውም ዘወር በሉ፥ የእስራኤልንም ቅዱስ ከእኛ ዘንድ አስወግዱ ይሉአቸዋል። 12ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ይህችን ቃል አቃልላችኋልና፥ በግፍና በጠማምነት ታምናችኋልና፥ በእርሱም ተደግፋችኋልና 13ስለዚህ ይህ በደል አዘብዝቦ ለመፍረስ እንደ ቀረበ፥ አፈራረሱም ፈጥኖ ድንገት እንደሚመጣ እንደ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል። 14የሸክለኛ ማድጋ እንደሚሰበር ይሰብረዋል፥ ሳይራራም ያደቅቀዋል፥ ከስባሪውም እሳት ከማንደጃ የሚወስዱበት ወይም ውኃ ከጕድጓድ የሚቀዱበት ገል አይገኝም። 15የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፥ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፥ እናንተም እምቢ አላችሁ፥ 16ነገር ግን፦ በፈረስ ላይ ተቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም አላችሁ፥ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፥ ደግሞም፦ በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን አላችሁ፥ ስለዚህም የሚያሳድዱአችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ። 17ከአንድ ሰው ዛቻ የተነሣ ሺህ ሰዎች ይሸሻሉ፥ እናንተም በተራራ ራስ ላይ እንዳለ ምሰሶ፥ በኮረብታም ላይ እንዳለ ምልክት ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፥ ከአምስት ሰዎች ዛቻ የተነሣ ትሸሻላችሁ። 18እግዚአብሔርም የፍርድ አምላክ ነውና ስለዚህ እግዚአብሔር ይራራላችሁ ዘንድ ይታገሣል፥ ይምራችሁም ዘንድ ከፍ ከፍ ይላል፥ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው። 19በኢየሩሳሌም ውስጥ በጽዮን የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅስም፥ በጩኸትም ድምፅ ይራራልሃል፥ በሰማህም ጊዜ ይመልስልሃል። 20ጌታም የጭንቀትን እንጀራና የመከራን ውኃ ቢሰጥህም አስተማሪህ እንግዲህ ከአንተ አይሰወርም፥ ዓይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፥ 21ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ፦ መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ። 22በብርም የተለበጡትን የተቀረጹትን ምስሎችህን በወርቅም የተለበጡትን ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችህን ታረክሳለህ፥ እንደ ርኩስም ነገር ትጥላቸዋለህ፦ ወግዱ ትላቸውማለህ። 23በምድርም ለተዘራው ዘርህ ዝናብ ይሰጣል፥ ከምድርም ፍሬ የሚወጣ እንጀራ ወፍራምና ብዙ ይሆናል። በዚያም ቀን ከብቶችህ በሰፊ መስክ ይሰማራሉ፥ 24መሬትንም የሚያርሱ በሬዎችና አህዮች በመንሽና በወንፊት የነጻውን ጨው ጨው የሚለውን ገፈራ ይበላሉ። 25በታላቅም እልቂት ቀን ግንቦች በወደቁ ጊዜ እረጅሙ ተራራ ሁሉ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ ወንዞችና የውኃ ፈሳሾች ይሆናሉ። 26እግዚአብሔርም የሕዝቡን ስብራት በጠገነ ዕለት፥ መቅሰፍቱ የቈሰለውንም በፈወሰ ዕለት፥ የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ ብርሃን፥ የፀሐይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት እጥፍ ይሆናል። 27እነሆ፥ የእግዚአብሔር ስም ከሚነድድ ቍጣ ከሚትጐለጐልም ጢስ ጋር ከሩቅ ይመጣል፥ ከንፈሮቹም ቍጣን የሞሉ ናቸው፥ ምላሱም እንደምትበላ እሳት ናት፥ 28እስትንፋሱም አሕዛብን በአጥፊ ወንፊት ሊነፋቸው እንደሚያጥለቀልቅ እስከ አንገትም እንደሚደርስ ወንዝ ነው፥ በሕዝብም መንጋጋ የሚያስት ልጓም ይሆናል። 29ዝማሬ በተቀደሰች የዐውደ ዓመት ሌሊት አንደሚሆን ዝማሬ ይሆንላቸዋል፥ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ እስራኤል አምባ ይመጣ ዘንድ እንቢልታ ይዞ እንደሚሄድ ሰው የልብ ደስታ ይሆንላችኋል። 30እግዚአብሔርም ክቡር ድምፁን ያሰማል፥ የክንዱንም መውረድ በሚነድድ ቍጣውና በምትበላ እሳት ነበልባል በዐውሎ ነፋስም በወጨፎም በበረዶ ጠጠርም ይገልጣል። 31አሦርም በበትር ከመታው ከእግዚአብሔር ድምፅ የተነሣ ይደነግጣል። 32እግዚአብሔር በላዩ የሚወርድበት የታዘዘበቱ የበትር ድብደባ ሁሉ በከበሮና በመሰንቆ ይሆናል፥ በጦርነትም ክንዱን አንሥቶ ይዋጋቸዋል። 33ከቀድሞም ጀምሮ የማቃጠያ ስፍራ ተዘጋጅታለች፥ ለንጉሥም ተበጅታለች፥ ጥልቅና ሰፊም አድርጎአታል፥ እሳትና ብዙ ማገዶ ተከምሮአል፥ የእግዚአብሔርም እስትንፋስ እንደ ዲን ፈሳሽ ያቃጥለዋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 30: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ