ኦሪት ዘፍጥረት 37:20-36

ኦሪት ዘፍጥረት 37:20-36 አማ54

አሁንም ኑ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው፦ ክፋ አውሬም በላው እንላለን ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን። ሮቤልም ይህን ሰማ ከእጃቸውም አዳነው እንዲህም አለ፦ ሕይወቱን አናጥፋ። ሮቤል፦ ደም አታፍስሱ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት አላቸው እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲንም ሆነ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱ ቀሚሱን ገፈፋት ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ ዓይናቸውንም አንሥተው አዩ፥ እነሆም የእስማኤላውያን ነገዶች ወደ ግብፅ ለመውረድ ከገለዓድ መጡ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን ከርቤም ተጭነው ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድር ነውም? ኑ ለእስማኤላውያን እንሽጠው እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና የምድያም ነጋዶችም አለፈ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጕድጓድ አወጡት ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሀያ ብር ሸጡት እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። ሮቤልም ወደ ጕድጓድ ተመለሰ፥ እነሆም ዮሴፍ በጕድጓድ የለም ልብሱንም ቀደደ። ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፦ ብላቴናውም የለም እንግዲህ እኔ ወዴት እሄዳለሁ? አለ። የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። ብዙ ኅብር ያለበት ቀሚሱንም ላኩ፥ ወደ አባታቸውም አገቡት እንዲህም አሉት፦ ይህንን አገኘነ ይህ የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እስኪ እየው። እርሱም አውቆ፦ የልጄ ቀሚስ ነውም ክፋ አውሬ በልቶታል ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል አለ ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። ወንዶች ልጆቹም ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሠ መጽናናትን እንቢ አለ እንዲህም አለ፦ ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ። እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብፅ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለዺጥፋራ ሸጡት።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}