ዘፍጥረት 37:20-36
ዘፍጥረት 37:20-36 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኑ፥ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው፤ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፤ ሕልሞቹም ምን እንደሚሆኑ እናያለን።” ሮቤልም ይህን ሰማ፤ ከእጃቸውም አዳነው፤ እንዲህም አለ፥ “ሕይወቱን አናጥፋ።” ሮቤልም፥ “ደም አታፍስሱ፤ በዚች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት፤ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት” አላቸው። ሮቤልም እንዲህ ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲህም ሆነ፤ ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺውን ቀሚሱን ገፈፉት፤ ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ባዶ ነበረ። እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ፤ ዐይኖቻቸውንም በአነሡ ጊዜ እነሆ፥ ይስማኤላውያን ነጋድያን ከገለዓድ ሲመጡ አዩ፤ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። ወደ ግብፅ ሀገርም ሊያራግፉ ይሄዱ ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፥ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድን ነው? ኑ፥ ለእነዚህ ይስማኤላውያን እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፤ ወንድማችን ሥጋችን ነውና።” ወንድሞቹም የነገራቸውን ሰሙት። እነዚያ ይስማኤላውያን ነጋዴዎችም ሲያልፉ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጕድጓድ ጐትተው አወጡት፤ ለይስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። ሮቤልም ወደ ጕድጓዱ ተመለሰ፤ እነሆም፥ ዮሴፍን ከጕድጓድ በአጣው ጊዜ ልብሱን ቀደደ። ሮቤልም ወደ ወንድሞቹ ተመልሶ፥ “ብላቴናው በጕድጓድ የለም፤ እንግዲህ እኔ ወዴት እሄዳለሁ?” አለ። የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፤ የፍየልም ጠቦት አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። ብዙ ኅብር ያለበትን ቀሚሱንም ላኩ፤ ወደ አባታቸውም አገቡት፤ እንዲህም አሉት፥ “ይህን ልብስ አገኘን፤ ይህ የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እስኪ እየው?” እርሱም ዐውቆ፥ “የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍን ቦጫጭቆታል” አለ። ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ፤ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ተሰብስበው መጡ። ኀዘኑንም ያስተዉት ዘንድ አባታቸውን ማለዱት። ኀዘኑንም መተውን እንቢ አለ፥ እንዲህም አላቸው፥ “ወደ ልጄ ወደ መቃብር እያዘንሁ እወርዳለሁ።” አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ። እነዚያ ይስማኤላውያን ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብፅ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጲጥፋራ ሸጡት።
ዘፍጥረት 37:20-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኑ እንግደለውና ከጕድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም፣ ‘ክፉ አውሬ ነጥቆ በላው’ እንላለን፤ እስኪ ሕልሞቹ ሲፈጸሙ እናያለን!” ሮቤል ግን ይህን ምክር ሲሰማ ከእጃቸው ሊያድነው ፈለገ፤ እንዲህም አለ፣ “ሕይወቱ በእጃችን አትለፍ፤ የሰው ደም አታፍስሱ፤ እዚህ ምድረ በዳ፣ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት እንጂ እጃችሁን አታንሡበት።” ሮቤል ይህን ያለው ሕይወቱን ከእጃቸው አትርፎ ወደ አባቱ ሊመልሰው ዐስቦ ነበር። ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደ ደረሰ፣ የለበሳትን በኅብረ ቀለማት ያጌጠች እጀ ጠባቡን ገፈፉት፤ ይዘውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውሃ የሌለበት ደረቅ ነበር። ምግባቸውን ለመብላት ተቀመጡ፤ አሻግረው ሲመለከቱም ከገለዓድ የሚመጡ እስማኤላውያን ነጋዴዎች የግመል ጓዝ አዩ። ነጋዴዎቹ ሽቱ፣ በለሳን ከርቤ በግመሎቻቸው ጭነው ወደ ግብጽ የሚወርዱ ነበሩ። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን መግደልና አሟሟቱን መደበቅ ምን ይጠቅመናል? ከዚህ ይልቅ ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በርሱ ላይ አናንሣ። ምንም ቢሆንኮ ወንድማችን፣ ሥጋችን ነው” ወንድሞቹም በሐሳቡ ተስማሙ። የምድያም ነጋዴዎችም እነርሱ ዘንድ እንደ ደረሱ፣ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጕድጓድ አውጥተው ለእስማኤላውያን በሃያ ጥሬ ብር ሸጡላቸው፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት። ሮቤል ወደ ጕድጓዱ ተመልሶ ሲያይ፣ ዮሴፍን በማጣቱ ልብሱን በሐዘን ቀደደ። ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፣ “ብላቴናው ጕድጓድ ውስጥ የለም፤ የት አባቴ ልሂድ?” አለ። ከዚያም የዮሴፍን እጀ ጠባብ ወሰዱ፤ አንድ ፍየልም ዐርደው እጀ ጠባቡን በደሙ ነከሩት። በኅብረ ቀለማት ያጌጠችውን እጀ ጠባብ ወደ አባታቸው ወስደው፣ “ይህን ወድቆ አገኘነው፤ የልጅህ እጀ ጠባብ መሆን አለመሆኑን እስኪ እየው” አሉት። እርሱም ልብሱን ዐውቆት፣ “ይህማ የልጄ እጀ ጠባብ ነው! ክፉ አውሬ በልቶታል፤ በርግጥም ዮሴፍ ተቦጫጭቋል” አለ። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለብሶ ስለ ልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት መጡ፤ እርሱ ግን ሊጽናና ባለመቻሉ “በሐዘን እንደ ተኰራመትሁ ልጄ ወዳለበት መቃብር እወርዳለሁ” አለ። ስለ ልጁም አለቀሰ። በዚህ ጊዜ፣ የምድያም ነጋዴዎች ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወስደው፣ ከፈርዖን ሹማምት አንዱ ለነበረው ለዘበኞች አለቃ፣ ለጲጥፋራ ሸጡት።
ዘፍጥረት 37:20-36 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁንም ኑ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው፦ ክፋ አውሬም በላው እንላለን ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን። ሮቤልም ይህን ሰማ ከእጃቸውም አዳነው እንዲህም አለ፦ ሕይወቱን አናጥፋ። ሮቤል፦ ደም አታፍስሱ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት አላቸው እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲንም ሆነ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱ ቀሚሱን ገፈፋት ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ ዓይናቸውንም አንሥተው አዩ፥ እነሆም የእስማኤላውያን ነገዶች ወደ ግብፅ ለመውረድ ከገለዓድ መጡ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን ከርቤም ተጭነው ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድር ነውም? ኑ ለእስማኤላውያን እንሽጠው እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና የምድያም ነጋዶችም አለፈ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጕድጓድ አወጡት ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሀያ ብር ሸጡት እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። ሮቤልም ወደ ጕድጓድ ተመለሰ፥ እነሆም ዮሴፍ በጕድጓድ የለም ልብሱንም ቀደደ። ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፦ ብላቴናውም የለም እንግዲህ እኔ ወዴት እሄዳለሁ? አለ። የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። ብዙ ኅብር ያለበት ቀሚሱንም ላኩ፥ ወደ አባታቸውም አገቡት እንዲህም አሉት፦ ይህንን አገኘነ ይህ የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እስኪ እየው። እርሱም አውቆ፦ የልጄ ቀሚስ ነውም ክፋ አውሬ በልቶታል ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል አለ ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። ወንዶች ልጆቹም ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሠ መጽናናትን እንቢ አለ እንዲህም አለ፦ ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ። እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብፅ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለዺጥፋራ ሸጡት።
ዘፍጥረት 37:20-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኑ እንግደለውና ከእነዚህ ጒድጓዶች በአንደኛው ውስጥ እንጣለው፤ ከዚህ በኋላ ‘ክፉ አውሬ በላው’ ብለን ማመኻኘት እንችላለን፤ በዚህ ዐይነት የሕልሙን መጨረሻ እናያለን” አሉ። ሮቤል ይህንን በሰማ ጊዜ ከእጃቸው ለማዳን በመፈለግ “ተዉ፤ አይሆንም፤ ባንገድለው ይሻላል፤ ከምትገድሉት ይልቅ በዚህ በበረሓ ባለው ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት” አላቸው። ሮቤል ይህን ያለው ከእጃቸው አድኖ ወደ አባቱ ሊመልሰው ፈልጎ ነው። ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በደረሰ ጊዜ ጌጠኛ የሆነውን እጀ ጠባቡን አወለቁበት፤ ዮሴፍንም ወስደው ውሃ በሌለው ደረቅ ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት። ከዚህ በኋላ ምሳ ለመብላት ተቀመጡ፤ በሚመገቡበትም ጊዜ እስማኤላውያን ነጋዴዎችን በሩቅ አዩ፤ እነርሱም በግመሎቻቸው ቅመማ ቅመም፥ በለሳን፥ ከርቤም ጭነው ከገለዓድ ወደ ግብጽ የሚጓዙ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ይሁዳ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን ገድለን የአሟሟቱን ሁኔታ ብንደብቅ ምን ይጠቅመናል? እርሱ የሥጋ ወንድማችን ስለ ሆነ” በእርሱ ላይ ጒዳት ከምናደርስበት ይልቅ ለእነዚህ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ብንሸጠው ይሻላል፤ ወንድሞቹም በዚህ ሐሳብ ተስማሙ። የምድያም ነጋዴዎች የሆኑ እስማኤላውያን በዚያ በኩል ያልፉ ነበር፤ ስለዚህ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጒድጓድ ጐትተው በማውጣት ለእነዚህ እስማኤላውያን በሃያ ብር ሸጡላቸው፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይዘውት ሄዱ። ሮቤል ወደ ጒድጓድ መጥቶ ዮሴፍ በዚያ አለመኖሩን ባወቀ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ወደ ወንድሞቹም ሄደና “እነሆ፥ ልጁ እዚያ የለም! እንግዲህ እኔ ወዴት ብሄድ ይሻለኛል?” አለ። ከዚህ በኋላ አንድ ፍየል ዐረዱና የዮሴፍን ልብስ በደም ነከሩት። ብዙ ኅብር ያለበትንም ልብሱን ወደ አባታቸው ወስደው “እነሆ፥ ይህን አገኘን የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እይ” አሉት። እርሱም የልጁ ልብስ መሆኑን ተረድቶ “በእርግጥ የእርሱ ልብስ ነው! አንድ ክፉ አውሬ ገድሎታል፤ ልጄን ዮሴፍን አውሬ ቦጫጭቆ በልቶታል!” አለ። ከዚህ በኋላ ልብሱን በሐዘን ቀደደ፤ ማቅ በወገቡ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀኖች አለቀሰ። ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ሊያጽናኑት ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱ ግን “ለልጄ እያለቀስሁ ወደ ሙታን ዓለም እወርዳለሁ” በማለት መጽናናትን እምቢ አለ። ስለዚህ ስለ ልጁ ማዘኑን ቀጠለ። በዚያን ጊዜ የምድያም ሰዎች እስማኤላውያን ዮሴፍን በግብጽ አገር ለጶጢፋር ሸጡት፤ ጶጢፋር ከፈርዖን ባለሥልጣኖች አንዱ የሆነ የዘበኞቹ አለቃ ነበር።
ዘፍጥረት 37:20-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኑ፥ እንግደለውና በአንዱ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው፦ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፥ የሕልሞቹን መጨረሻ እናያለን።” ሮቤልም ይህን ሲሰማ፥ “ሕይወቱን አናጥፋ” በማለት ከእጃቸው አዳነው። “ደም አታፍስሱ፥ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጉድጓድ ጣሉት፥ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት” አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲህም ሆነ፥ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፥ ወስደውም ወደ ጉድጓድ ጣሉት፥ ጉድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። ምግብ ሊበሉ ተቀመጡ፥ ዓይናቸውንም አንሥተው ሲያዩ፥ እነሆ የእስማኤላውያን ነጋዴዎች ወደ ግብጽ ለመውረድ ከገለዓድ ይመጣሉ፥ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድነው? ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና።” ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት። የምድያም ነጋዶችም አለፉ፥ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጉድጓድ አወጡት፥ ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት፥ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት። ሮቤል ወደ ጉድጓዱ በተመለሰ ጊዜ፥ እነሆ ዮሴፍ በጉድጓድ የለም፥ ልብሱንም ቀደደ። ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፦ “ብላቴናው የለም፤ እኔስ ወዴት ልሂደው?” አለ። የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፥ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። ብዙ ኅብር ያለበትንም ልብሱን ወደ አባታቸው ወስደው “እነሆ፥ ይህን አገኘን የልጅህ ልብስ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ እይ” አሉት። እርሱም ለይቶ ስላወቀው፦ “የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል” አለ። ያዕቆብ ልብሱንም ቀደደ፥ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፥ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ፦ “ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ።” አባቱም እንደዚህ ስለ እርሱ አለቀሰ። እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብጽ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጶጥፋራ ሸጡት።