በግምባሬም አጎነበስሁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገድሁ፤ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። አሁንም ቸርንትና እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ። ላባና ባቱኤልም መለሱ እንዲህም አሉ፦ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአል ክፉም በጎ፥ ልንመልስልህ አንችልም ርብቃ እንኍት በፊትህ ናት ይዘሃት ሂድ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን። የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ ልብስም አወጣ፥ ለርብቃም ሰጣት፤ የከበረ ስጦታንም ለወንድምዋና ለእናትዋ አቀረበ። እርሱም ከእርሱም ጋር ያሉት በሉ ጠጡም ከዚያም አደሩ ማልደውም ተነሡና፦ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው። ወንድምዋና እናትዋም፦ ብላቴናይቱ አንድ አሥር ቀን ያህል እንኳ ከእኛ ዘንድ ትቀመጥ ከዚያም በኍላ ትሄዳለች አሉ። እርሱም፦ እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው። እነርሱም፦ ብላቴናቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ አሉ። ርብቃንም ጠርተው፦ ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን? አሉአት። እርስዋ፦ እሄዳለሁ አለች። እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚትዋንም የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው። ርብቃንም መረቁአትና፦ አንቺ እኅታችን እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ አሉአት። ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም በግመሎችም ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት፤ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ። ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ በሚሉአት ምንጭ መንገድ መጣ በአዜብ ምድር ተቀምጦ ነበርና። ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር ዓይኖቹንም፥ አቀና እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች ይስሐቅንም አየች ከግመልም ወረድች። ሎሌውንም፦ ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው? አለችው። ሎሌውም፦ እርሱ ጌታዬ ነው አላት እርስዋም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች። ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት ርብቃንም ወሰዳት ሚስትም ሆነችው ወደዳትም ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና።
ኦሪት ዘፍጥረት 24 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 24:48-67
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች