ከዚህ በኋላ ለጌታዬ ልጅ ሚስት የምትሆነዋን ሴት ወዳገኘሁበት ወደ ጌታዬ ወንድም ቤት በቀና መንገድ ለመራኝ ለእግዚአብሔር በጒልበቴ ተንበርክኬ ሰገድሁ፤ የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንኩ፤ እንግዲህ የጌታዬን ዐደራ በእውነት ተቀብላችሁ እርሱን ደስ ለማሰኘት የምትፈቅዱ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ የማትፈቅዱም እንደ ሆነ ቊርጡን ንገሩኝ፤ እኔም እግዚአብሔር ወደሚመራኝ እሄዳለሁ።” ላባና ባቱኤልም “ይህ ነገር ከእግዚአብሔር የመጣ ስለ ሆነ፥ መከልከል አንችልም፤ ርብቃ ይህችውልህ፤ እነሆ፥ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር ራሱ እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁን” አሉት። የአብርሃም አገልጋይ ይህን በሰማ ጊዜ በጒልበቱ ተንበርክኮ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጌጣጌጦችን፥ እንዲሁም ልብስ አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ለወንድምዋና ለእናትዋም በጣም ውድ የሆኑ ስጦታዎችን አውጥቶ ሰጣቸው። ከዚህ በኋላ የአብርሃም አገልጋይና አብረውት የነበሩ ሰዎች በልተው ጠጥተው እዚያው ዐደሩ፤ ጠዋት በተነሡ ጊዜ የአብርሃም አገልጋይ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ ፍቀዱልኝ” አለ። ነገር ግን የርብቃ ወንድምና እናትዋ “ልጅትዋ ዐሥር ቀን ያኽል ከእኛ ጋር ትቈይ፤ ከዚያ በኋላ ከአንተ ጋር ልትሄድ ትችላለች” አሉት። እርሱ ግን “እባካችሁ አታቈዩኝ፤ እግዚአብሔር የመጣሁበትን ጉዳይ ስላቃናልኝ ቶሎ ብዬ ወደ ጌታዬ ልመለስ” አላቸው። እነርሱም “እስቲ ልጅቷን እንጥራና እርስዋ የምትለውን እንስማ” አሉ። ስለዚህ ርብቃን ጠሩና “ከዚህ ሰው ጋር መሄድ ትፈልጊያለሽን?” ብለው ጠየቅዋት። እርስዋም “አዎ እሄዳለሁ” አለች። ስለዚህ ርብቃ ሞግዚትዋን አስከትላ፥ ከአብርሃም አገልጋይና ከእርሱ ሰዎች ጋር እንድትሄድ ፈቀዱላት። “አንቺ እኅታችን የብዙ ሺህ ሕዝብ እናት ሁኚ፤ ዘሮችሽም የጠላቶቻቸውን ከተሞች ይውረሱ!” ብለው ርብቃን መረቁአት። ከዚህ በኋላ ርብቃ ከደንገጡሮችዋ ጋር ለመሄድ ተነሣች፤ በግመሎቹ ላይ ተቀምጠው ከአብርሃም አገልጋይ ጋር ለመሄድ ተዘጋጁ። በዚህ ዐይነት የአብርሃም አገልጋይ ርብቃን ይዞ ሄደ። በዚህ ጊዜ ይስሐቅ “ብኤር ላሐይ ሮኢ ወይም የሚያየኝ ሕያው አምላክ” የተባለው ኲሬ ወዳለበት በረሓ መጥቶ በኔጌብ ተቀምጦ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ማታ ጊዜ እያሰላሰለ በመስክ ውስጥ ሲዘዋወር ሳለ ግመሎች ሲመጡ በሩቅ አየ። ርብቃ ይስሐቅን ባየች ጊዜ ከግመሏ ወረደችና፥ “ያ በመስክ ውስጥ ወደ እኛ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል የአብርሃምን አገልጋይ ጠየቀችው። አገልጋዩም “እርሱ ጌታዬ ነው” አላት። ስለዚህ በፍጥነት በሻሽ ፊትዋን ሸፈነች። አገልጋዩም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። ከዚህ በኋላ ይስሐቅ እናቱ ሣራ ትኖርበት ወደነበረው ድንኳን ርብቃን ይዞአት ገባ፤ ሚስትም ሆነችው፤ ይስሐቅ ርብቃን ወደዳት፤ በእናቱ ሞት ምክንያት ከደረሰበትም ሐዘን በዚህ ሁኔታ ተጽናና።
ኦሪት ዘፍጥረት 24 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 24:48-67
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች