ዘፍጥረት 24:48-67
ዘፍጥረት 24:48-67 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህንም ነገር ከአንደበቷ በሰማሁ ጊዜ እጅግ ደስ አሰኘችኝ። ለጆሮዎችዋም ጉትቻዎችን ለእጆችዋም አምባሮችን አድርጌ አስጌጥኋት። ደስ ባሰኘችኝም ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር ሰገድሁ፤ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። አሁንም ቸርነትንና እውነትን ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ፤ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እመለስ ዘንድ። ባቱኤልና ላባም መለሱ፤ እንዲህም አሉ፥ “ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአል፤ ክፉ ወይም በጎ ልንመልስልህ አንችልም። ርብቃ እንኋት፤ በፊትህ ናት፤ ይዘሃት ሂድ፥ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁን።” የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ፥ ልብስም አወጣ፤ ለርብቃም ሰጣት፤ ዳግመኛም ለአባቷና ለእናቷ እጅ መንሻ ሰጣቸው። ከዚህም ሁሉ በኋላ እርሱ፥ ከእርሱ ጋር ያሉትም በሉ፤ ጠጡም፤ በዚያም አደሩ፤ በማለዳም ተነሥቶ፥ “ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ” አላቸው። አባቷ እናቷና ወንድምዋ፦ “ብላቴናዪቱ ዐሥር ቀን ያህል እንኳ በእኛ ዘንድ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ትሄዳለች” አሉ። እርሱም፥ “እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኝ ሳለ አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ” አላቸው። እነርሱም፥ “ብላቴናዪቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ” አሉ። ርብቃንም ጠርተው፥ “ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን?” አሉአት። እርስዋም፥ “አዎን እሄዳለሁ” አለች። እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚቷንም ከገንዘብ ጋር፥ የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው። እኅታቸው ርብቃንም መረቁአትና፥ “አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላት ሀገሮችን ይውረስ” አሉአት። ርብቃም ተነሣች፤ ደንገጥሮችዋም፥ በግመሎችዋ ላይ ተቀምጠው ከሰውዬው ጋር አብረው ሄዱ፤ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ። ይስሐቅም በዐዘቅተ ራእይ በኩል ወደ ምድረ በዳ ይመለከት ነበር፤ በአዜብ በኩል ባለው ምድር ተቀምጦ ነበርና። ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር፤ ዓይኖቹንም አቀና፤ እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ። ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች፤ ይስሐቅንም አየች፤ ከግመልም ወረደች። ሎሌውንም፥ “ሊቀበለን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማነው?” አለችው። ሎሌውም፥ “እርሱ ጌታዬ ነው” አላት፤ እርስዋም ቀጸላዋን ወስዳ ተከናነበች። ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። ይስሐቅም ወደ እናቱ ቤት ገባ፤ ርብቃንም ወሰዳት፤ ሚስትም ሆነችው፤ ወደዳት፤ ይስሐቅም ስለ እናቱ ስለ ሣራ ተጽናና።
ዘፍጥረት 24:48-67 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ተደፍቼም ለእግዚአብሔር ሰገድሁ፤ ለጌታዬ ወንድም የልጅ ልጅ የሆነችውን ቈንጆ፣ ለጌታዬ ልጅ እንዳገኝለት በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬ የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። እንግዲህ አሁን ለጌታዬ በጎነትና ታማኝነት የምታሳዩ ከሆነ ሐሳባችሁን አስታውቁኝ፤ ካልሆነ ግን ቍርጡን ንገሩኝና የምሄድበትን ልወስን።” ላባና ባቱኤል እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ነገሩ ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ በዚህም ሆነ በዚያ ምንም ማለት አንችልም። ርብቃ ይቻትልህ፤ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁነው።” የአብርሃም አገልጋይ ያሉትን በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ። ከዚያም የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ እንዲሁም ልብሶች አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ደግሞም ለወንድሟና ለእናቷ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች ሰጣቸው። እርሱና ዐብረውት የነበሩ ሰዎችም በልተው፣ ጠጥተው እዚያው ዐደሩ። በማግስቱም ጧት ሲነሡ፣ የአብርሃም አገልጋይ፣ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አለ። ወንድሟና እናቷም፣ “ልጅቷ ከእኛ ጋራ ቢያንስ ዐሥር ቀን ያህል ትቈይና ከዚያ በኋላ ልትሄድ ትችላለች።” ብለው መለሱ። እርሱ ግን፣ “እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አላቸው። እነርሱም፣ “ለማንኛውም ልጅቱን እንጥራትና ትጠየቅ” አሉ። ስለዚህ ርብቃን ጠርተው፣ “ከዚህ ሰው ጋራ መሄድ ትፈቅጃለሽ?” ሲሉ ጠየቋት። እርሷም፣ “አዎን፤ እሄዳለሁ” አለች። ከዚያም እኅታቸውን ርብቃን ከሞግዚቷ ጋራ፣ እንዲሁም የአብርሃምን አገልጋይና ዐብረውት የነበሩትን ሰዎች አሰናበቷቸው። ርብቃንም እንዲህ ብለው መረቋት፤ “እኅታችን ሆይ፤ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽ የጠላቶቹን ደጆች ይውረስ”። ከዚያም ርብቃና አገልጋዮቿ ተዘጋጁ፤ ግመሎቻቸውም ላይ ወጥተው ሰውየውን ተከተሉት፤ በዚህ ሁኔታ አገልጋዩ ርብቃን ይዟት ሄደ። በዚህ ጊዜ፣ ይሥሐቅ በኔጌብ ይኖር ስለ ነበር፣ ከብኤርላሃይሮኢ መጥቶ ነበር። ይሥሐቅም አንድ ምሽት ላይ በጥሞና ለመቈየት ወደ መስክ ወጣ አለ፤ ቀና ብሎ ሲመለከትም፣ ግመሎች ከሩቅ ሲመጡ አየ። ርብቃም እንደዚሁ አሻግራ ስትመለከት፣ ይሥሐቅን አየች፤ ከግመልም ወረደች፤ አገልጋዩንም፣ “ይህ ሊገናኘን በመስኩ ውስጥ ወደዚህ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው። አገልጋዩም፣ “ጌታዬ ነው” ብሎ መለሰላት፤ እርሷም መሸፈኛዋን ተከናነበች። አገልጋዩም ያደረገውን ሁሉ ለይሥሐቅ ነገረው። ይሥሐቅም ርብቃን ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን ይዟት ገባ፤ አገባት፣ ሚስትም ሆነችው፤ እርሱም ወደዳት። ይሥሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና።
ዘፍጥረት 24:48-67 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በግምባሬም አጎነበስሁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገድሁ፤ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። አሁንም ቸርንትና እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ። ላባና ባቱኤልም መለሱ እንዲህም አሉ፦ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአል ክፉም በጎ፥ ልንመልስልህ አንችልም ርብቃ እንኍት በፊትህ ናት ይዘሃት ሂድ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን። የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ ልብስም አወጣ፥ ለርብቃም ሰጣት፤ የከበረ ስጦታንም ለወንድምዋና ለእናትዋ አቀረበ። እርሱም ከእርሱም ጋር ያሉት በሉ ጠጡም ከዚያም አደሩ ማልደውም ተነሡና፦ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው። ወንድምዋና እናትዋም፦ ብላቴናይቱ አንድ አሥር ቀን ያህል እንኳ ከእኛ ዘንድ ትቀመጥ ከዚያም በኍላ ትሄዳለች አሉ። እርሱም፦ እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው። እነርሱም፦ ብላቴናቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ አሉ። ርብቃንም ጠርተው፦ ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን? አሉአት። እርስዋ፦ እሄዳለሁ አለች። እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚትዋንም የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው። ርብቃንም መረቁአትና፦ አንቺ እኅታችን እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ አሉአት። ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም በግመሎችም ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት፤ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ። ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ በሚሉአት ምንጭ መንገድ መጣ በአዜብ ምድር ተቀምጦ ነበርና። ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር ዓይኖቹንም፥ አቀና እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች ይስሐቅንም አየች ከግመልም ወረድች። ሎሌውንም፦ ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው? አለችው። ሎሌውም፦ እርሱ ጌታዬ ነው አላት እርስዋም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች። ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት ርብቃንም ወሰዳት ሚስትም ሆነችው ወደዳትም ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና።
ዘፍጥረት 24:48-67 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ለጌታዬ ልጅ ሚስት የምትሆነዋን ሴት ወዳገኘሁበት ወደ ጌታዬ ወንድም ቤት በቀና መንገድ ለመራኝ ለእግዚአብሔር በጒልበቴ ተንበርክኬ ሰገድሁ፤ የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንኩ፤ እንግዲህ የጌታዬን ዐደራ በእውነት ተቀብላችሁ እርሱን ደስ ለማሰኘት የምትፈቅዱ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ የማትፈቅዱም እንደ ሆነ ቊርጡን ንገሩኝ፤ እኔም እግዚአብሔር ወደሚመራኝ እሄዳለሁ።” ላባና ባቱኤልም “ይህ ነገር ከእግዚአብሔር የመጣ ስለ ሆነ፥ መከልከል አንችልም፤ ርብቃ ይህችውልህ፤ እነሆ፥ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር ራሱ እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁን” አሉት። የአብርሃም አገልጋይ ይህን በሰማ ጊዜ በጒልበቱ ተንበርክኮ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጌጣጌጦችን፥ እንዲሁም ልብስ አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ለወንድምዋና ለእናትዋም በጣም ውድ የሆኑ ስጦታዎችን አውጥቶ ሰጣቸው። ከዚህ በኋላ የአብርሃም አገልጋይና አብረውት የነበሩ ሰዎች በልተው ጠጥተው እዚያው ዐደሩ፤ ጠዋት በተነሡ ጊዜ የአብርሃም አገልጋይ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ ፍቀዱልኝ” አለ። ነገር ግን የርብቃ ወንድምና እናትዋ “ልጅትዋ ዐሥር ቀን ያኽል ከእኛ ጋር ትቈይ፤ ከዚያ በኋላ ከአንተ ጋር ልትሄድ ትችላለች” አሉት። እርሱ ግን “እባካችሁ አታቈዩኝ፤ እግዚአብሔር የመጣሁበትን ጉዳይ ስላቃናልኝ ቶሎ ብዬ ወደ ጌታዬ ልመለስ” አላቸው። እነርሱም “እስቲ ልጅቷን እንጥራና እርስዋ የምትለውን እንስማ” አሉ። ስለዚህ ርብቃን ጠሩና “ከዚህ ሰው ጋር መሄድ ትፈልጊያለሽን?” ብለው ጠየቅዋት። እርስዋም “አዎ እሄዳለሁ” አለች። ስለዚህ ርብቃ ሞግዚትዋን አስከትላ፥ ከአብርሃም አገልጋይና ከእርሱ ሰዎች ጋር እንድትሄድ ፈቀዱላት። “አንቺ እኅታችን የብዙ ሺህ ሕዝብ እናት ሁኚ፤ ዘሮችሽም የጠላቶቻቸውን ከተሞች ይውረሱ!” ብለው ርብቃን መረቁአት። ከዚህ በኋላ ርብቃ ከደንገጡሮችዋ ጋር ለመሄድ ተነሣች፤ በግመሎቹ ላይ ተቀምጠው ከአብርሃም አገልጋይ ጋር ለመሄድ ተዘጋጁ። በዚህ ዐይነት የአብርሃም አገልጋይ ርብቃን ይዞ ሄደ። በዚህ ጊዜ ይስሐቅ “ብኤር ላሐይ ሮኢ ወይም የሚያየኝ ሕያው አምላክ” የተባለው ኲሬ ወዳለበት በረሓ መጥቶ በኔጌብ ተቀምጦ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ማታ ጊዜ እያሰላሰለ በመስክ ውስጥ ሲዘዋወር ሳለ ግመሎች ሲመጡ በሩቅ አየ። ርብቃ ይስሐቅን ባየች ጊዜ ከግመሏ ወረደችና፥ “ያ በመስክ ውስጥ ወደ እኛ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል የአብርሃምን አገልጋይ ጠየቀችው። አገልጋዩም “እርሱ ጌታዬ ነው” አላት። ስለዚህ በፍጥነት በሻሽ ፊትዋን ሸፈነች። አገልጋዩም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። ከዚህ በኋላ ይስሐቅ እናቱ ሣራ ትኖርበት ወደነበረው ድንኳን ርብቃን ይዞአት ገባ፤ ሚስትም ሆነችው፤ ይስሐቅ ርብቃን ወደዳት፤ በእናቱ ሞት ምክንያት ከደረሰበትም ሐዘን በዚህ ሁኔታ ተጽናና።
ዘፍጥረት 24:48-67 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በግምባሬም አጎነበስሁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገድሁ፥ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። አሁንም ቸርነትና እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደሆነ ንገሩኝ፥ ይህም ባይሆን ንገሩኝ፥ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ።” ላባና ባቱኤልም መለሱ እንዲህም አሉ፦ “ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቷል ክፉም በጎም ልንመልስልህ አንችልም። ርብቃ እነኋት በፊትህ ናት፥ ይዘሃት ሂድ፥ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን።” የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ ልብስም አወጣ፥ ለርብቃም ሰጣት፥ የከበረ ስጦታንም ለወንድምዋና ለእናትዋ አቀረበ። እርሱም ከእርሱም ጋር ያሉት በሉ ጠጡም፥ ከዚያም አደሩ፥ ማልደውም ተነሡና፦ “ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ” አላቸው። ወንድምዋና እናትዋም፦ “ብላቴናይቱ አንድ ዐሥር ቀን ያህል እንኳ ከእኛ ዘንድ ትቀመጥ፥ ከዚያም በኋላ ትሄዳለች” አሉ። እርሱም፦ “እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፥ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ” አላቸው። እነርሱም፦ “ብላቴናይቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ” አሉ። ርብቃንም ጠርተው፦ “ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን?” አሉአት። እርሷም፦ “እሄዳለሁ” አለች። እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚትዋንም የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው። ርብቃንም መረቁአትና፦ “አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ፥ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ” አሉአት። ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም፥ በግመሎችም ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት፥ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ። ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ በሚሉአት ምንጭ መንገድ መጣ፥ በአዜብ ምድር ተቀምጦ ነበርና። ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር፥ ዐይኖቹንም አቀና፥ እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ። ርብቃም ዐይኖችዋን አቀናች፥ ይስሐቅንም አየች፥ ከግመልም ወረደች። ሎሌውንም፦ “ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው?” አለችው። ሎሌውም፦ “እርሱ ጌታዬ ነው” አላት፥ እርሷም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች። ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት፥ ርብቃንም ወሰዳት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወደዳትም፥ ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና።