ዘፍጥረት 24:48-67

ዘፍጥረት 24:48-67 NASV

ተደፍቼም ለእግዚአብሔር ሰገድሁ፤ ለጌታዬ ወንድም የልጅ ልጅ የሆነችውን ቈንጆ፣ ለጌታዬ ልጅ እንዳገኝለት በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬ የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። እንግዲህ አሁን ለጌታዬ በጎነትና ታማኝነት የምታሳዩ ከሆነ ሐሳባችሁን አስታውቁኝ፤ ካልሆነ ግን ቍርጡን ንገሩኝና የምሄድበትን ልወስን።” ላባና ባቱኤል እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ነገሩ ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ በዚህም ሆነ በዚያ ምንም ማለት አንችልም። ርብቃ ይቻትልህ፤ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁነው።” የአብርሃም አገልጋይ ያሉትን በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ። ከዚያም የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ እንዲሁም ልብሶች አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ደግሞም ለወንድሟና ለእናቷ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች ሰጣቸው። እርሱና ዐብረውት የነበሩ ሰዎችም በልተው፣ ጠጥተው እዚያው ዐደሩ። በማግስቱም ጧት ሲነሡ፣ የአብርሃም አገልጋይ፣ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አለ። ወንድሟና እናቷም፣ “ልጅቷ ከእኛ ጋራ ቢያንስ ዐሥር ቀን ያህል ትቈይና ከዚያ በኋላ ልትሄድ ትችላለች።” ብለው መለሱ። እርሱ ግን፣ “እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አላቸው። እነርሱም፣ “ለማንኛውም ልጅቱን እንጥራትና ትጠየቅ” አሉ። ስለዚህ ርብቃን ጠርተው፣ “ከዚህ ሰው ጋራ መሄድ ትፈቅጃለሽ?” ሲሉ ጠየቋት። እርሷም፣ “አዎን፤ እሄዳለሁ” አለች። ከዚያም እኅታቸውን ርብቃን ከሞግዚቷ ጋራ፣ እንዲሁም የአብርሃምን አገልጋይና ዐብረውት የነበሩትን ሰዎች አሰናበቷቸው። ርብቃንም እንዲህ ብለው መረቋት፤ “እኅታችን ሆይ፤ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽ የጠላቶቹን ደጆች ይውረስ”። ከዚያም ርብቃና አገልጋዮቿ ተዘጋጁ፤ ግመሎቻቸውም ላይ ወጥተው ሰውየውን ተከተሉት፤ በዚህ ሁኔታ አገልጋዩ ርብቃን ይዟት ሄደ። በዚህ ጊዜ፣ ይሥሐቅ በኔጌብ ይኖር ስለ ነበር፣ ከብኤርላሃይሮኢ መጥቶ ነበር። ይሥሐቅም አንድ ምሽት ላይ በጥሞና ለመቈየት ወደ መስክ ወጣ አለ፤ ቀና ብሎ ሲመለከትም፣ ግመሎች ከሩቅ ሲመጡ አየ። ርብቃም እንደዚሁ አሻግራ ስትመለከት፣ ይሥሐቅን አየች፤ ከግመልም ወረደች፤ አገልጋዩንም፣ “ይህ ሊገናኘን በመስኩ ውስጥ ወደዚህ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው። አገልጋዩም፣ “ጌታዬ ነው” ብሎ መለሰላት፤ እርሷም መሸፈኛዋን ተከናነበች። አገልጋዩም ያደረገውን ሁሉ ለይሥሐቅ ነገረው። ይሥሐቅም ርብቃን ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን ይዟት ገባ፤ አገባት፣ ሚስትም ሆነችው፤ እርሱም ወደዳት። ይሥሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}