ኦሪት ዘፍጥረት 23:1-20

ኦሪት ዘፍጥረት 23:1-20 አማ54

የሣራም ዕድሜ መቶ ሀያ ሰባት ዓመት ሆነ። በቂርያትአርባቅም ሞተች፤ እርስዋም በከነዓን ምድር ያለች ኬብሮን ናት አብርሃምም ለሣራ ሊያዝንላትን ሊያለቅስላት ተነሣ። አብርሃምም ከሬሳው አጠገብ ተነሣ። ለኬጢ ልጆችም እንዲህ ሲል ተናገረ፦ እኔ በእናንተ ዘንድ ስደተኛና መጻተኛ ነኝ በእናንተ ዘንድ የመቃብር ርስት ስጡኝ፥ ሬሳዬንም ከፊቴ ልቅበር። የኬጢ ልጆችም ለአብርሃም መለሱ፥ አሉትም፦ ጌታ ሆይ ስማን፤ አንተ በእኛ መካከለ ከእግዚአብሔር አለቃ ነህ ከመቃብር ስፍራችን በመልካሙ ቦታ ሬሳህን ቅበር፤ ሬሳህን ትቀብር ዘንድ ከእኛ መቃብሩን የሚከለክልህ የለም። አብርሃምም ተነሣ ለምድሩ ሕዝብም ለኬጢ ልጆች ሰገደ። እንዲህም አላቸው፦ ሬሳዬን ከፊቴ እንድቀብር ከወደዳችሁስ ስሙኝ ከሰዓር ልጅ ከኤፍሮንም ለምኑልኝ፤ በእርሻው ዳር ያለውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን በሙሉ ዋጋ በመካከላችሁ ይስጠኝ፥ መቃብሩ የእኔ ርስት እንዲሆን። ኤፍሮን፥ በኬጢ ሰው ኤፍሮን፥ የኬጢ ልጆችና ወደ ከተማ የሚገቡ ሁሉ ሲሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ አይደለም ጌታዬ ስማኝ። እርሻውን ሰጥቼሃለሁ በእርሱም ዳር ያለውን ዋሻ ሰጥቼሃለሁ፤ በወገኔ ልጆች ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሳህን ቅበር። አብርሃምም በአገሩ ሰዎች ፊት ሰገደ፤ የአገሩ ሰዎችም ሲሰሙ ለኤፍሮን እንዲህ ሲል ተናገረ፦ ነገሬን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የእርሻውን ዋጋ እሰጥሃለሁ አንተም ከእኔ ዘንድ ውሰድ፥ ሬሳዬም፥ በዚይ እቀብራለሁ። ኤፍሮን፥ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ ጌታዬ ሆይ እኔን ስማኝ፤ የአራት መቶ ሰቅል ዋጋ ምድር በእኔና በአንተ መካክለ ምንድር ነው? ሬሳህንም ቅበር። አብርሃምም የኤፍሮንን ነገር ሰማ አብርሃምም በኬጢ ልጆች ፊት የነገረውን አራት መቶ ሰቅል መዝኖ ለኤፍሮን ሰጠው ብሩም ለመሸጫ ለመለወጫ የሚተላለፍ ነበረ። በመምሬ ፊት ያለው ባለድርብ ክፍል የሆነው የኤፍሮን እርሻ ለአብርሃም ጸና፤ እርሻው በእርሱም ያለው እንጨት ሁሉ በኬጢ ልጆችና በከተማይቱ በር በሚገቡ ሁሉ ፊት ለአብርሃም ርስቱ ሆነ። ከዚህም በኍላ ኬብሮን በምትባል በመምሬ ፊት በከነዓን ምድር ባለው እርሻ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ አብርሃም ሚስቱን ሣራን ቀበረ። እርሻውና በእርሱ ያለው ዋሻው በኬጢ ልጆች ዘንድ ለአብርሃም የመቃብር ርስት ሆኖ ጸና።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}