ሣራ መቶ ኻያ ሰባት ዓመት ከኖረች በኋላ፥ በከነዓን ምድር ባለችው “ቂርያት አርባዕ” ተብላ በምትጠራው በኬብሮን ከተማ ሞተች፤ አብርሃም በሣራ ሞት ምክንያት እጅግ አዘነ፤ አለቀሰም። የሚስቱ አስከሬን ካለበት ስፍራ ተነሥቶ ወደ ሒታውያን ሄደና፥ “እኔ በመካከላችሁ በእንግድነት የምኖር ስደተኛ ነኝ፤ እባካችሁ የመቃብር ቦታ ሽጡልኝ፤ የሚስቴንም አስከሬን በዚያ ልቅበር” አላቸው። ሒታውያንም እንዲህ ብለው መለሱለት፥ “ጌታው፥ እስቲ ስማን፤ አንተ በመካከላችን እንደ ታላቅ መስፍን ነህ፤ ከመቃብሮቻችን ጥሩውን መርጠህ የሚስትህን አስከሬን እዚያ ቅበር፤ ሁላችንም ብንሆን የሚስትህን አስከሬን የምትቀብርበት መቃብር ልንሰጥህ ፈቃደኞች ነን” አሉት። ከዚህ በኋላ አብርሃም በሒታውያን ፊት እጅ ነሥቶ እንዲህ አለ፤ “የሚስቴን አስከሬን እዚህ እንድቀብር ከፈቀዳችሁልኝ የጾሐር ልጅ ዔፍሮን፥ በእርሻው ድንበር ላይ ያለችውን ማክፌላ የተባለችውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻ እንዲሸጥልኝ ጠይቁልኝ፤ ይህ ስፍራ የመቃብር ቦታ እንዲሆንልኝ በእናንተ ፊት ሙሉ ዋጋ ከፍዬ እንድገዛው አድርጉልኝ።” ዔፍሮን ራሱ በከተማው በር አጠገብ በነበረው መሰብሰቢያ ስፍራ ከሌሎች ሒታውያን ጋር ተቀምጦ ነበር፤ ስለዚህ እዚያ የነበሩት ሰዎች ሁሉ እየሰሙ እንዲህ አለ፤ “ጌታው ስማ፤ እርሻውን በክልሉ ውስጥ ካለው ዋሻ ጋር ሰጥቼሃለሁ፤ ሙታንህን እንድትቀብርበት በወገኖቼ በሒታውያን ፊት ሰጥቼሃለሁ።” አብርሃም ግን በሒታውያን ፊት እንደገና እጅ ነሣና፥ ሁሉም እየሰሙ ዔፍሮንን “እባክህ አድምጠኝ፤ ቦታውን በሙሉ እገዛዋለሁ፤ እነሆ ዋጋውን ተቀበለኝና የሚስቴን አስከሬን እዚያ ወስጄ ልቅበር” አለው። ዔፍሮንም አብርሃምን እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታዬ የመሬቱ ዋጋ አራት መቶ ብር ቢሆን ነው፤ ታዲያ ይህ በእኔና በእናንተ መካከል ምንድን ነው? ይልቅስ የሚስትህን አስከሬን እዚህ ቅበር።” አብርሃምም በነገሩ ተስማምቶ ዔፍሮን በሕዝቡ ፊት በተናገረው መሠረት በነጋዴዎች ሚዛን ልክ አራት መቶ ብር መዝኖ ሰጠው። በዚህ ዐይነት ከመምሬ በስተምሥራቅ ማክፌላ የተባለው የዔፍሮን ቦታ የአብርሃም ርስት ሆነ፤ ይህም ቦታ እርሻውን፥ በውስጡ ያለውን ዋሻና በእርሻው ክልል ውስጥ ያለውን ዛፍ ሁሉ ያጠቃልላል። በዚያም ተገኝተው የነበሩት ሒታውያን ሁሉ የአብርሃም ርስት መሆኑን አረጋገጡ። ከዚህ በኋላ አብርሃም በከነዓን ምድር ባለችው በዚህችው ዋሻ የሚስቱን የሣራን አስከሬን ቀበረ፤ ስለዚህ የሒታውያን የነበረው እርሻ በውስጡ ካለው ዋሻ ጋር የአብርሃም የመቃብር ርስት ሆነ።
ኦሪት ዘፍጥረት 23 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 23:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos