ኦሪት ዘፍጥረት 21:8-21

ኦሪት ዘፍጥረት 21:8-21 አማ54

ሕፃኑም አደገ ጡትንም ከመጥባት ተቋረጠ፤ አብርሃምም ይስሐቅን ጡት ባስጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣን አደረገ። ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው። አብርህምንም፤ ይህችን ባሪያ ከነልጅዋ አሳድድ የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና አለችው። ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው ስለ ባሪያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፤ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና። የባሪያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ ዘርህ ነውና። አብርሃምም ማልዶ ተነሣ እንጀራንም ወሰደ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትክሻው አሸከማት ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት እርስዋም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቀበዘበዘች። ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፤ ብላቴናውንም ከአንድ ቍጥቋጦ በታች ጣለችው እርስዋም ሄደች፥ ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፥ አጋር ሆይ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና። እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት የውኃ ጕድጓድንም አየች ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች ብላቴናውንም አጠጣች። እግዚአብሔርም ከብላቴናው ጋር ነበረ፤ አደገም በምድረ በዳም ተቀመጠ፥ ቀስተኛም ሆነ። በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፤ እናቱም ከምድረ ግብፅ ሚስት ወሰደችለት።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}