ዘፍጥረት 21:8-21

ዘፍጥረት 21:8-21 NASV

ሕፃኑ አደገ፤ ጡት መጥባቱንም ተወ። አብርሃምም ይሥሐቅ ጡት በጣለባት ዕለት ታላቅ ድግስ ደገሰ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብጻዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል በይሥሐቅ ላይ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤ አብርሃምንም፣ “ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርራት፤ የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይሥሐቅ ጋራ አይወርስምና” አለችው። እስማኤል ልጁ ስለ ሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው። እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ ሐሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይሥሐቅ በኩል ስለ ሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ። የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለ ሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።” በማግስቱም አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሟት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር። በእርኮት የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ፣ ልጁን ከአንድ ቍጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው። ከዚያም፣ “ልጁ ሲሞት ዐይኔ አያይም” ብላ፣ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ዐረፍ አለች፤ እርሷም እየተንሰቀሰቀች ታለቅስ ጀመር። እግዚአብሔርም የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ። ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጕድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች። እግዚአብሔር ከልጁ ጋራ ነበር፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ መኖሪያውንም በምድረ በዳ ውስጥ አደረገ፤ ጐበዝ ቀስተኛም ሆነ። በፋራን ምድረ በዳ ሳለም፣ እናቱ ከግብጽ አንዲት ሴት አምጥታ አጋባችው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}