ኦሪት ዘፍጥረት 17:1-14

ኦሪት ዘፍጥረት 17:1-14 አማ54

አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆን ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና፥ እነሆ ኤልሻዳይ ነኝ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጽምም ሁን፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ አለው። አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁም ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኍላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ኪፋን አቆማለሁ፥ ለአንተና ለአንተ በኍላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር የከነዓ ምድር ሁሉ ለዘላለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኍላ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቅለህ፥ አንተ ከአንተም በኍላ ዘርህ በትውልዳቸው። በእኔና በአንተ መካከለ ከአንተም በኍላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔን ይህ ነው ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆንል። የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ፥ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገርዝ። በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ። ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘላለም ቃል ኪዳን ይሆናል። የቍልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቆላፍ ሰው ሁሉ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}