ኦሪት ዘፍጥረት 17:1-14

ኦሪት ዘፍጥረት 17:1-14 አማ05

አብራም 99 ዓመት በሆነው ጊዜ እግዚአብሔር ተገለጠለትና “እኔ ኤልሻዳይ ሁሉን የምችል አምላክ ነኝ፤ ለእኔ በመታዘዝ ዘወትር ትክክል የሆነውን ነገር አድርግ፤ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ዘርህንም እጅግ አበዛዋለሁ” አለው። አብራም ግንባሩ መሬት እስኪነካ ድረስ ዝቅ ብሎ ሰገደ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ከአንተ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፤ የብዙ ሕዝቦች አባት አደርግሃለሁ፤ የብዙ ሕዝቦች አባት ስለማደርግህም ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ አብራም መሆኑ ቀርቶ አብርሃም ይሆናል። እጅግ ብዙ ሕዝቦች እስኪሆኑ ዘሮችህን አበዛቸዋለሁ፤ ከእነርሱም መካከል ነገሥታት የሚሆኑ ይገኛሉ። “በአንተና በዘርህ፥ በመጪውም ትውልድ መካከል ቃል ኪዳኔን ለዘለዓለም አጸናለሁ፤ በዚህም ዐይነት ለአንተና ከአንተ በኋላ ለሚመጣው ዘርህ አምላክ እሆናለሁ። አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን ይህችን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣችኋለሁ፤ መላውን የከነዓን ምድር ለዘለዓለም እንዲወርሱት ለዘርህ እሰጣለሁ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።” እንደገናም እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “አንተና ከአንተም በኋላ የሚመጣው ዘርህ ከእኔ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን ከትውልድ እስከ ትውልድ ጠብቁ፤ አንተና ከአንተ በኋላ የሚመጣው ዘርህ የምትጠብቁት ቃል ኪዳን ይህ ነው፤ በመካከላችሁ ያሉት ወንዶች ሁሉ መገረዝ አለባቸው፤ ሸለፈታችሁን ትገረዛላችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል፤ በመጪው ዘመን የሚወለድ ወንድ ልጅ ሁሉ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ይገረዝ፤ እንዲሁም በቤትህ የተወለዱና በቤትህ ሳይወለዱ ከውጪ በገንዘብ ተገዝተው የመጡ ባሪያዎች ሳይቀሩ በዚሁ ዐይነት ይገረዙ። ቃል ኪዳኔ ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር የሚኖር መሆኑን የሚያሳይ የሥጋ ምልክት እንዲሆን እያንዳንዱ ወንድ ይገረዝ። በሥጋው ያልተገረዘ ወንድ ሁሉ ቃል ኪዳኔን ስላላከበረ ከሕዝቡ ይወገዳል።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}