የይሁዳና የብንያምም ጠላቶች ምርኮኞቹ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መቅደስ እንደ ሠሩ ሰሙ። ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶች ቤቶች አለቆች ቀርበው “የአሦር ንጉሥ አስራዶን ወደዚህ ካመጣን ቀን ጀምሮ ለአምላካችሁ እንሠዋለንና፥ እንደ እናንተም እንፈልገዋለንና ከእናንተ ጋር እንሥራ” አሉአቸው። ዘሩባቤልና ኢያሱም የቀሩትም የእስራኤል አባቶች ቤቶች አለቆች “የአምላካችንን ቤት መሥራት ለእኛና ለእናንተ አይደለም፤ እኛ ለብቻችን ግን የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዳዘዘን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት እንሠራለን” አሉአቸው። የምድሩም ሕዝብ የይሁዳን ሕዝብ እጅ ያደክሙ ነበር፤ እንዳይሠሩም አስፈራሩአቸው፤ ምክራቸውንም ያፈርሱ ዘንድ በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ ዘመን ሁሉ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት ድረስ መካሪዎችን ገዙባቸው። በጠረክሲስ መንግሥት፥ በመንግሥቱም በመጀመሪያ ዘመን፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ላይ የክስ ነገር ጻፉ። በአርጤክስስም ዘመን ቢሽላም፥ ሚትሪዳጡ፥ ጣብኤልና ተባባሪዎቹ ለፋርስ ንጉሥ ለአርጤክስስ ጻፉ፤ ደብዳቤውም በሶርያ ፊደልና በሶርያ ቋንቋ ተጽፎ ነበር። አዛዡ ሬሁም እና ጸሐፊው ሲምሳይ በኢየሩሳሌም ላይ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ። አዛዡ ሬሁም እና ጸሐፊው ሲምሳይ፥ የቀሩትም ተባባሪዎቻቸው፥ ዲናውያን፥ አፈርሳትካውያን፥ ጠርፈላውያን፥ አፈርሳውያን፥ አርካውያን፥ ባቢሎናውያን፥ ሱስናካውያን፥ ዴሐውያን፥ ኤላማውያን፥ ታላቁና ኃይለኛው አስናፈር ያፈለሳቸው፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶ ያኖራቸው እና የቀሩትም አሕዛብ ደብዳቤውን ጻፉ። ለንጉሡ ለአርጤክስስ የላኩት የደብዳቤ ግልባጭ ይህ ነው “በወንዝ ማዶ ያሉት ሰዎች ባሪያዎችህ፤ አሁንም ከአንተ ዘንድ የወጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጡ ንጉሡ ይወቅ፤ ዓመፀኛይቱንና እጅግም የከፋችቱን ከተማ ይሠራሉ፤ ቅጥርዋንም ያድሳሉ፤ መሠረትዋንም ይጠግናሉ። አሁንም ይህች ከተማ የተሠራች እንደ ሆነ፥ ቅጥርዋም የታደሰ እንደ ሆነ፥ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይሰጡ፥ የንጉሡም ገቢው እንዲጐድል ንጉሡ ይወቅ። የንጉሡንም ጨው እንበላለንና፥ ንጉሡንም ሲያቃልሉት ማየት አይገባንምና ስለዚህ ልከን ለንጉሡ አስታውቀናል፤ በአባቶችህ ታሪክ መጽሐፍ ምርመራ ይደረግ፤ በዚያም በታሪክ መጽሐፍ ይህች ከተማ ዓመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጐዳች፥ ከጥንቱም ሽፍትነት በእርስዋ እንደ ተጀመረ ታገኛለህ፤ ታውቃለህም፤ ስለዚህም ይህች ከተማ ፈርሳ ነበር። ይህችም ከተማ የተሠራች እንደ ሆነ፥ ቅጥርዋም የታደሰ እንደ ሆነ፥ በወንዝ ማዶ ክፍል እንደሌለህ ለንጉሡ እናስታውቃለን።”
መጽሐፈ ዕዝራ 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዕዝራ 4:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች